ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ ብዝሃነቶቻችንን አቅፎ የሚይዝና የሚያስተናግድ የፌዴራል ስርዓት ወሳኝ ነው-አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ለጠንካራ ሃገረ መንግስት ግንባታ ብዝሃነቶቻችንን አቅፎ የሚይዝና የሚያስተናግድ የፌዴራል ስርዓት ወሳኝ ነው-አቶ አገኘሁ ተሻገር
ሀዋሳ ህዳር 29/2015 (ኢዜአ) ብዝሃነትን ያከበረ የፌዴራል ስርዓት ለመገንባት በተቀናጀ መልኩ የተጀመረውን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
የዘንድሮው 17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሀዋሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።
አፌ ጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ያሉንን ብዝሃነቶች አቅፎ የሚይዝና የሚያስተናግድ ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ብዝሃነት በአግባቡ የሚያስተናግድ ስርዓት ባለመገንባቱ ለሚፈጠሩ ቁርሾዎችና ላለመግባባቶች ምክንያት እየሆነ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ይህን ለማጥፋትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ባለፉት አራት ዓመታት መንግስት እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት ለመተግበር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህም በዚህ ልክ እየተከበረ የሚገኘው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸው ይህ ሂደት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ምሁራን የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ብዝሃነቶቻችን በአግባቡ ተስተናግደው የምንመኘውን ብልጽግና ለማረጋገጥና የተጀመረውን ጥረት ለማሳካት እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ለበዓሉ ድምቀትም ሚናቸውን ሲወጡ ለነበሩት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።