ቀጥታ፡

ያሉንን ብዝኃ እሴቶች በመጠበቅ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል- አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ ህዳር 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) ያሉንን ብዝኃ እሴቶች በመጠበቅ አንድነታችንን ልናጠናክርና ሀገራችንን ልንገነባ ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

17ኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ-ቃል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በሀዋሳ ስታዲየም እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ ያሉንን በርካታ ብዝሃነቶችን በአግባቡ በመያዝ የውስጥ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ብለዋል።

ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ያሉንን ጸጋዎች የማልማትና የመጠቀም ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።

ሊከፋፍሉን የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ሀይሎችን እኩይ ዓላማ በመረዳት በህብረ ብሄራዊነት የተገነባችና ሰላሟ የተራጋገጠ ሀገርን ለመገንባት ሁሉም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ህብረ ብሄራዊነታችንን ማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማታችን አቅም በመሆኑ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በበዓሉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም