ቀጥታ፡

የፌዴራል ሥርዐቱ ስኬታማ እንዲሆን ህብረብሔራዊነትና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን መሰረት ማድረግ እንዳለበት ተጠቆመ

ሀዋሳ (ኢዜአ).ህዳር 28/2015 የፌዴራል ሥርዐቱ ስኬታማ እንዲሆን ህብረብሔራዊነትና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን መሰረት ያደረገ አተገባበር ሊኖረው እንደሚገባ ተመለከተ።

17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በማስመልከት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ተካሂዷል።

በሲምፖዚየሙ ላይ በፌዴራሊዝም ፅንሰ ሀሳብ፣ ተሞክሮዎች፣ ሀገራዊ አፈፃፀምና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራሊዝም አስተምህሮ ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር ኃይለኢየሱስ ታዬ ባቀረቡት ጽሁፍ የፌዴራል ስርዓት የፖለቲካ ፍልስፍና መሆኑን አመልክተዋል።

በፌዴራል ሥርዐት ተመርተው ስኬታማና ጠንካራ ሀገረ-መንግስት መገንባት የቻሉ ህዝቦች እንዳሉ ሁሉ የከሰሙ ፌዴሬሽኖች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የስኬትና ውድቀታቸው መንስኤዎች በዋናነት ከዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ከማንነትና ራስን በራስ ከማስተዳደር እንዲሁም ተያያዥ መብቶች ጋር ትስስር እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው የፌዴራል ሥርዐት ስኬታማ እንዲሆን ብዝሀነትን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያስተናግድ አተገባበር ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል ።

መሰረታዊ የሆኑ የዜጎች ሰብዐዊ መብቶች በአግባቡ ሊከበሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሌላው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህር ዶክተር ከይረዲን ተዘራ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመለከቱት በተለይ ከለውጡ በፊት የነበረው የፌዴራል ሥርዐት አተገባበር ኢትዮጵያ የተሰራችበትን የአንድነት ገመድ በወጉ ያልተመለከተና ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ነጠላ ማንነት ላይ ያጠነጠነ እንደነበር ተናግረዋል ።

ዶክተር ከይረዲን ኢትዮጵያዊያን ለረጅም ጊዜ የተገነባ ተሰባጥሮ የመኖር፣ ተመሳሳይ የሆነ የዕርቀ ሠላምና የሽምግልና ሥርዐቶች፣ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ያለመደራደር የጋራ ማንነት እንዳላቸው አውስተዋል።

ሲተገበር የቆየው የፌዴራል ሥርዐት እነዚህን መገለጫዎቻችንን በወጉ ያላየ በመሆኑ የተረጋጋ ሥርዐተ መንግስት መገንባት ሳይቻል መቅረቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በህብረብሔራዊነት የተቃኘ የፌዴራል ሥርዐት መከተል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

17ኛው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ነገ በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም