ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የምታደርገው ድጋፍ የሚደነቅ ነው--የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር

ህዳር 28 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሐመድ ኑር፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግሥት እና ሕዝብን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ ስታደርግ የቆየችውና እያደረገች ያለችው ድጋፍ የሚደነቅ ተግባር ነው ሲሉ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሐመድ ኑርን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሩ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያና የሶማሊያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ኢትዮጵያ የሶማሊያ መከላከያ ሠራዊት አቅምን ለማጎልበት በሥልጠናና በአቅም ግንባታ ረገድ ተከታታይ ድጋፎችን እንድታደርግ ጠይቀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ አሸባሪውን የአልሸባብ ኃይል በመደምሰስ እና የሶማሊያን ሰላም እና መረጋጋት ለማረጋገጥ በመደበኛ ስምሪትና በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ሠራዊት በማሰማራት ከፍተኛ መሥዋዕትነት ስትከፍል መቆየቷን ገልጸዋል።

በዚህ መሥዋዕትነትም በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ማግኘት በመቻሉ ፀረ-አልሸባብ ትግሉ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሌሎች አጋር አገራት ጋር በመሆን በሶማሊያ የምታደርገው ፀረ አልሸባብ ትግል ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት ድርሻው የጎላ መሆኑን የገለጹት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህንን ትግል ውጤታማ ለማድረግ የሁለቱ ሀገራት በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከመደበኛና ከሰላም አስከባሪ የሠራዊት ስምሪት በተጨማሪ የሶማሊያ መከላከያ ኃይልና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች አቅማቸውን ማሳደግና አስተማማኝ አቅም መፍጠር እንዲችሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እና አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርግም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።

የመጀመሪያ ቀን የሥራ ጉብኝቱን ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ያደረገው በሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሐመድ ኑር የተመራው የልዑካን ቡድን በቀጣይ ቀናት ከመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ጋርም ውይይት እንደሚያደርግ ከመከላከያ ሠራዊት ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም