ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል-አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል-አቶ አደም ፋራህ
ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 28 ቀን 2015 ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህና የሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ነገ በሚከበረው 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ለመታደም ዛሬ ሀዋሳ ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
በዚህ ወቅት አቶ አዳም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ችግር በሰላም ስምምነት መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።
17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የሰላም ስምምነት በመፈራረም ችግሩ በተፈታበት ወቅት የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁለንተናዊ የብልጽግና ጉዞን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰላም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችለው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት፣ በፍትሀዊነት፣ በወንድማማችነትና እህትማማችነት በጋራ ሲኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር አካታች ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት የዘንድሮ በዓል መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በሀዋሳ በሚከበረው 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ለመታደም ሲመጡ ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብትና እኩልነታቸውን አክብሮ ጠንካራ አንድነት በመገንባት ዘላቂ ሰላማችንን ማረጋገጥ እጅግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን በሚገልጽና ከፍ በሚያደርግ መልኩ በዓሉ ለማክበር ስንመጣ ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል ከልብ ማመስገን እወዳለሁ ብለዋል ከንቲባዋ።