ቀጥታ፡

በዓሉ ባህልና ማንነታችንን በአደባባይ ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን ያጠናክራል-የበዓሉ ታዳሚዎች

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 28 ቀን 2015 ''የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ባህልና ማንነታችንን በአደባባይ ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን ያጠናክራል'' ሲሉ በዓሉ ታዳሚዎች ተናገሩ።

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በነገው ዕለት በሲዳማ ክልል አዘጋጅነት በሀዋሳ ከተማ በልዩ ልዩ ክንውኖች ይከበራል።

በዓሉ ላይ ለመታደም ሀዋሳ ከተማ ያገኘናቸው ከደቡብ፣ ከደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ እና ከአማራ ክልል የመጡ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች ቀኑ መከበሩ የሕዝቦችን መስተጋብር ያጠናክራል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የባህልና ታሪክ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለተቀረው ዓለም ለማሳየትና ለማስተዋወቅ በዓሉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ወጣት ቦሮሌ ጎራሼ የበዓሉ መከበር የኢትዮጵያ ህዝቦችን ባህል፣ ታሪክና ቅርስ በአንድ መድረክ ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሯል።

አቶ ድንበሩ ደርቤ በበኩላቸው በዓሉ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ላይ የሚገናኙበት መድረክ በመሆኑ እለቱን በናፍቆት እንደሚጠብቁት ይናገራሉ።

''በርካታ አንድ የሚያደርጉንና የጋራ የሆኑ ማንነቶች ስላሉን በዓሉ እርስ በርስ የሚያቀራርበን ወሳኝ መድረክ ነው'' ብለዋል።

የዚህችዓለም አባት በበኩሏ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ በሚታዋወቁበትና አንድነታቸውን በሚያጠናክሩበት በዓል መታደም በመቻሏ ደስታዋን ገልጸለች።

በዓሉ ላይ የወከለችውን አካባቢ ለማስተዋወቅ መዘጋጀቷንም ተናግራለች።

የበዓሉ መከበርም የህዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና ፍቅር ለማጠናከርና ለማጽናት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም