ቀጥታ፡

በአፍሪካ ለሚያጋጥሙ የሠላምና ፀጥታ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ማበጀት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መንገድ ነው- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

ህዳር 28/2015 (ኢዜአ) በአፍሪካ ለሚያጋጥሙ የሠላምና ፀጥታ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ማበጀት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መንገድ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

በአፍሪካ አህጉር ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክረው 9ኛው ከፍተኛ የአፍሪካ ሠላምና ፀጥታ ጉባዔ በአልጄሪያ ኦራን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባዔው ላይ እየተሳተፈ ነው።

ጉባዔው የአፍሪካ ህብረት የፀጥታው ምክር ቤት አባል አገራት እንዲሁም A3 በመባል የሚታወቀው አፍሪካን በመወከል በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆነው እያገለገሉ ያሉ አገራት በምክር ቤቱ በተለይ የአፍሪካ ሀገራትን ፍላጎትና ጥቅም በብቃት ማስጠበቅ በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ እየመከረ ነው ።

በጉባዔው ላይ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ ማብራርያ ሰጥተዋል።

በማብራርያቸው በኢትዮጵያ ላይ በውጭ ሃገራት ጣልቃ ገብነት ጫና በበረታበት ወቅት በተመድ አፍሪካን ወክለው ለተሳተፉ ሀገራት ከኢትዮጵያና ከፍትህ ጎን በመቆም ላሳዩት ጠንካራ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደር ብርቱካን በአፍሪካ ለሚያጋጥሙ የሠላምና ፀጥታ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ማበጀት ፤ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አይነተኛ መንገድ እንደሆነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በወቅቱ አፍሪካን በመወከል በተመድ ፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆነው እያገለገሉ ያሉ ሃገራት ኬንያ፣ ጋና፣ጋቦን ሲሆኑ፤ ከአውሮፓውያኑ ጥር 2023 ጀምሮ ሞዛምቢክ የቆይታ ጊዜዋን የምታጠናቅቀውን ኬንያ በመተካት አባልነቱን ትቀላቀላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም