ቀጥታ፡

ሙስናን በመታገል ፍትሃዊ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሰፍን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 28/2015 ሙስናን በመታገል ፍትሃዊ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሰፍን ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአገልግሎት እና መልካም አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ አለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ዓለም አቀፉን የጸረ-ሙስና ቀን እና 17ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አክብረዋል፡፡   

የጽህፈት ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች በዚሁ ጊዜ እንደ አገር በልማት ስራዎች ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች ሙስናን እና የተደራጀ ሌብነትን በመታገል መድገም ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ሙስናን መታገል ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ሙስና የአገር ነቀርሳ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላምን በማደፍረስ የአገር ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ በመሆኑ መታገል ይገባል ብለዋል፡፡

ዜጎች ሙሰኞችን በማጋለጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተው ኢትዮጵያውያን በበርካታ የልማት ስራዎች ያሳዩትን ትብብር ሙስናን በመታገል መድገም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያ ውበትና የእድገት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

ዜጎች ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅረበዋል፡፡

በመድረኩ የሙስናን አስከፊነት በማስመልክት ጽሁፍ ያቀረቡት ወይዘሮ ጽጌ ብርሃኑ ሙስና ልማትን የሚያዳክም፣ የኢኮኖሚ እደገት እንዲገታ እንዲሁም የሞራል እና የስነ-ምግባር ቀውስ እንዲባባስ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም