የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ከእስራኤል በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት ለተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ከእስራኤል በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት ለተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 28/2015 ብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ከእስራኤል በመጡ ባለሙያዎች አማካኝነት በአደጋ መከላከልና ጸረ-ሽብርተኝነት ዙሪያ ለተለያዩ ተቋማት ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።
በስልጠናው ከመከላከያ ሰራዊት፣ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከኢትዮጵያ አቬሽን ባለስልጣን፣ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ስልጠናው ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ፤ በነገው እለት እንደሚጠናቀቅም ነው የተገለጸው፡፡
ስልጠናው በአደጋ መከላከልና ፀረ-ሽብርተኝነት እንዲሁም በቀውስ አስተዳደር ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤና ተሞክሮ እንዲወስዱ እንዳደረጋቸው ነው የስልጠናው ተሳታፊዎች የተናገሩት፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስን ወክለው በስልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙት ኮማንደር አስጨናቂ አሰፋ፤ ስልጠናው በተለይ በቀውስ አስተዳደር ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲዳብር እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን የመጡት ታዬ ጋቢሳ በበኩላቸው ስልጠናው በቀውስ አስተዳደር የነበሩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እንዲሁም ያሉ ክፍተቶችን ለማሻሻል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በስልጠናው በቀውስ ጊዜ ተቋማት በምን መልኩ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ልምድ የሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ከጤና ሚኒስቴር የመጡት ዶክተር ገነት ክፍሌ ናቸው፡፡
ስልጠናውን ከሚሰጡት አሰልጣኞች መካከል ዶሮን ሃደር እንዳሉት፤ ስልጠናው በዋናነት በአደጋ መከላከልና ጸረ-ሽብርተኝነት ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ይህም የተሻሉ ልምዶችን በማካፈል የሁለቱ አገራትን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡