ከሞሮኮ 218 ሺህ 894 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል - ኢዜአ አማርኛ
ከሞሮኮ 218 ሺህ 894 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጂቡቲ ወደብ ይደርሳል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 28/2015 በኢትዮጵያ ለሚመረተው የበጋ ስንዴ ምርት የሚውል 218 ሺህ 894 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጓጉዞ ጂቡቲ ወደብ የሚደርስ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ከመነሻ እስከ ወደብ፤ ከባህር ወደብ እስከ መጋዘን እንዲሁም ለአርሶ አደሩ በፍጥነት ለማድረስ እያጓጓዘ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ድርጅቱ ቀልጣፋ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ነው፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎቱን በራሱ ማጓጓዝ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞቹን ፍላጎት ማርካት ችሏል ብለዋል፡፡
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ከወጭ ቅነሳና ውጤታማ አገልግሎት ከመስጠት አንፃር ለዓለም ይዘነው መቅረብ የምንችለው ልምድ አግኝተናል ሲሉም ተናግረዋል።
ዘንድሮም ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመጀመሪያው መርከብ ከሞሮኮ የሚመጣውን የአፈር ማዳበሪያ ጭኖ ተንቀሳቅሷል ብለዋል፡፡
በቀጣይም ተጨማሪ ሶስት ባለ ከፍተኛ ጭነት መርከቦች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 218 ሺህ 894 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ ላይ የሚያራግፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መንግስት በበጋ ስንዴ ምርት ላይ የጀመረውን መርሃ-ግብር ለማሳካት ከውጭ የሚገቡ የግብርና ግብዓቶችን በፍጥነት በሟጓጓዝ ለተልዕኮው መሳካት የድርሻችን መወጣታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በቀጣይም የግዥ ሂደት ላይ ያለው የአፈር ማዳበሪያ ሂደቱ እንደተጠናቀቀ በፍጥነት በማጓጓዝ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆን እንሰራልን ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ከጥር በፊት የሚገባ የአፈር ማዳበሪያ እንዳልነበረ አስታውሰው በአዲስ አሰራር ከአንድ ወር በፊት ቀድመን በማስገባት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንገኛለን ብለዋል።