ቀጥታ፡

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በነገው እለት በሐዋሳ ከተማ በድምቀት ይከበራል - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሐዋሳ(ኢዜአ) ህዳር 28/ 2015 17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ከፌዴራል እና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ተወካዮች በተገኙበት በነገው ዕለት በሐዋሳ ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ቀኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት የተረጋገጠበት በመሆኑ በደመቀ ሥነ ሥርዓት ይከበራል።

የፌዴራል ስርዓቱ ራስን በራስ እና ሀገርን በጋራ ማስተዳደር ያስቻለ ነው ያሉት አቶ ደስታ፤ ዜጎች የጋራ ጉዳያቸውን በሚመለከት በፌዴራል ስርዓት የሚተዳደሩበትና በየአካባቢያቸው ደግሞ ራሳቸውን የሚያስተዳደሩበትን ነፃነት ያቀዳጃቸው ነው ብለዋል።

ይህንን በመጠቀም በክልሎች መካከል የተጀመሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ተጠናክረው እና ጎልተው አንዲቀጥሉ በማስቻል ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይበልጥ እየጎለበተ እና የህዝቦች ቅርርብ እየደረጀ እንዲሄድ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተለይ በዓሉ ማንነታችንና መልካምነታችንን የምንገልጽበትና የምናሳይበት፣ ከሌሎች ወንድምና እህቶቻችን ጋር ይበልጥ የምንተዋወቅበት በመሆኑ በዓሉን ባማረና በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ የበዓሉ ታዳሚዎችን እየተቀበልን እንገኛለን ብለዋል።

May be an image of 3 people, people standing, outdoors and crowd

በአሁኑ ወቅት በዓሉን ለመታደም የገቡ እንግዶችም በሐዋሳ ከተማ በመንቀሳቀስ እየጎበኙና ባህላዊ ክንዋኔዎችን በመስቀል አደባባይ ለህዝቡ እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች እንደሚታደሙበት ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ወደ ክልሉ የሚመጡ የክብር እንግዶቹንና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን በአክብሮት እሴት ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ጥሪ አቅርበዋል።

የሐዋሳ ከተማና አካባቢው ህዝብም በእለቱ በነቂስ በመሳተፍ ከእንግዶች ጋር በአንድነት በዓሉን በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንዲያከብር መልእክት አቅርበዋል።

May be an image of 1 person, sky and tree

የዘንድሮው በዓል ኢትዮጵያ ተግዳሮቶችን በድል ተሻግራ የተለያዩ ልማቶችን ማሳካት በጀመረችበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በነገው እለት በሀዋሳ ስታዲየም በሚከበረው በዓል ላይ የኢትዮጵያ የብሔሮች ብሔረሰቦች ባህል የሚያንፀባርቁ ዜማዎችን በማሰማትና ባህላዊ ውዝዋዜዎችን በማሳየት ለበዓሉ ድምቀት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም