በልማት ስራዎች ያስመዘገብነውን ስኬት ሙስናን እና የተደራጀ ሌብነትን በመታገል መድገም ይጠበቅብናል -የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አመራሮችና ሰራተኞች - ኢዜአ አማርኛ
በልማት ስራዎች ያስመዘገብነውን ስኬት ሙስናን እና የተደራጀ ሌብነትን በመታገል መድገም ይጠበቅብናል -የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አመራሮችና ሰራተኞች
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 28/2015 በበርካታ የልማት ስራዎች ያስመዘገብነውን ስኬት ሙስናን እና የተደራጀ ሌብነትን በመታገል መድገም ይጠበቅብናል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ገለጹ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ዓለም አቀፉን የጸረ-ሙስና ቀን እና 17ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አክብረዋል፡፡
የጽህፈት ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች በዚሁ ጊዜ ሙስና የአገር ልማት እና ህልውና ጠንቅ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በተግባር ሊታገለው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአገልግሎት እና መልካም አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ አለምፀሐይ ጳውሎስ ሙስና መታገል ለመንግስት ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዜጎች ሙሰኞችን በማጋለጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተው ኢትዮጵያውያን በበርካታ የልማት ስራዎች ያሳዩትን ትብብር ሙስናን በመታገል መድገም እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ዜጎች ህብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን በጋራ መስራት እንዳለባቸው የጽህፈት ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሚኒስትር ድኤታዋ አለምጸሃይ ጳውሎስ የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያ ውበትና የእድገት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የህዝቦችን አንድነት ለመሸርሸር የሚሰሩ ኃይሎችን በጋራ መታጋል ይገባል ብለዋል፡፡