ቀጥታ፡

በቀጣናው የሚስተዋሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው - የደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ፖሊስ ተቋማት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 28/2015 በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎችም አጎራባች አገራት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን የደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ፖሊስ ተቋማት ገለጹ።

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ያለው 24ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ጠቅላላ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከሩን ቀጥሏል።

ከስብሰባው ታዳሚዎች መካከል የደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ልዑክ መሪዎች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሽብርተኝነትንና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

የደቡብ ሱዳን ፖሊስ አገልግሎት የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ሳዲክ እስማኤል ሲዲጊ፤ ደቡብ ሱዳን ሽብርተኝነትን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ድንበር በምትዋሰንባቸው ሌሎች አካባቢዎች የጸጥታ ኃይል በማሰማራት የመከላከል ትብብሯን እንደምታጠናክርም አረጋግጠዋል።

ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) ሌሎች ተቋማትና አገራት ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኗን ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ በሽብር መከላከል ሥራ ላይ ያላት ልምድ ለብዙ አገራት ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቁመው በቀጣይ የጋራ ትብብራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኤርትራ ፖሊስ ተቋም ተወካይ እና የፖሊስ አካዳሚ መምህሩ ኮሎኔል ሐዲስ ስዩም ስብሰባው በአፍሪካ ቀንድ በሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል ግብዓት የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በቀጣይ ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም