ባለፈው አንድ ወር በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል

105

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27/2015 ባለፈው አንድ ወር በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

በመንግሥትና ህወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በጦርነቱ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች የሚወስዱ ሁሉም የሰብዓዊ ድጋፍ ኮሪደሮች ክፍት መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ገለጻ እንዳሉት ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ134 ሺህ 948 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብ አቅርቦት ወደ አካባቢዎቹ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

በዚህም በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ በአካባቢዎቹ 3 ሺህ 239 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግብ በማጓጓዝ ለ71 ሺህ 978 ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች መከፋፈሉን ተናግረዋል፡፡

እንደ ነዳጅ፣ መድኃኒት፣ የሕክምና መሳሪያዎች፣ የትምህርት ቁሳቁሶችና ሌሎች ምግብ-ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ መንግሥት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም