በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል-- ባለሥልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ሥራ ማከናወን ተችሏል-- ባለሥልጣኑ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27/2015 በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ሥራ ማከናወን መቻሉን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ባለሥልጣኑም በዋናነት የስፖርት አበረታች ቅመሞችን መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ግንዛቤ መፍጠር ላይ ይሰራል፡፡
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን መከላከልና መቆጣጠር በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬታማ ሥራ ተከናውኗል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ በዘርፉ በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ መድረኮች ተሞክሮዋን እንድታቀርብ መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡
ከዚህ አኳያ ባለሥልጣኑ ዓለም አቀፍ ትብብር በመፍጠር የትምህርትና ሥልጠና እንዲሁም በምርመራና ቁጥጥር የማስፈጸም አቅሙ እንዲሻሻል ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን የአበረታች ቅመሞች ሥራዎቹ ተገምግመው ዓለም አቀፍ ሕግና ደንብን የተከተሉ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
"ከዚህ በፊት የተሰሩ የስፖርት አበረታች ቅመሞች መከላከል ሥራዎች ለወደፊቱ ዋስትና አይሆኑም" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ዘላቂነት እንዲኖረው የተጠናከረ ሥራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ከ4 ሺህ ባላይ ለሚሆኑ አትሌቶች ምርምራ ተደርጎ 20 የሚሆኑት አበረታች መድኃኒቶችን ተጠቅመው መገኘታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ከሁለት ዓመት ጀምሮ እስከ እድሜ ልክ ውድድር መታገድ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ብለዋል፡፡
የአበረታች መድኃኒት ወስደው ከተገኙት አትሌቶች መካከል አብዛኞቹ መድኃኒቱን ባለማወቅ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም አትሌቶች የትኛውንም መድኃኒት ሲወስዱ ከባለሙያዎች ምክር መጠየቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አበረታች ቅመሞች በመውሰድ ቅጣት የተላለፈባቸው አትሌቶች ከውድድር መታገድ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ሽልማታቸውና ደመወዛቸው እንደሚታገድም ነው የጠቆሙት፡፡