በጎ ፈቃደኝነት አገራዊ ባህልና እሴት ሆኖ በዜጎች የእለት ተእለት መስተጋብር ውስጥ ሊተገበር ይገባል --ዶክተር ጀማሉ ጀምበሩ

157

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27 ቀን 2015  በጎ ፈቃደኝነት አገራዊ ባህልና እሴት ሆኖ በዜጎች የእለት ተእለት መስተጋብር ውስጥ ሊተገበር እንደሚገባ የአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኝነት ቀንን በማስመልከት በአዲስ አበባ ከተማ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የአዲስ አበባ ኅብረሰተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ጀማሉ ጀምበሩ፤ በውይይቱም በጎ ፈቃደኝነት ወሰን እና ድንበር የሌለው ሰብዓዊ አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኝነት ለሰው ልጅ በጎ ተግባር በመፈጸም የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በጎ ፈቃደኝነት በኢትዮጵያ ሰፊ መሰረት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤  ከዚህ አኳያ አገራዊ ባህልና እሴት ሆኖ እንዲቀጥል ሊደረግ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

ለበጎ ፈቃደኞች እውቅና ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች የማበረታቻ መንገዶችን በመተግበር በጎ ፈቃደኝነትን ማበረታታት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ ሥራቸው የሚታወቁት አቶ መሐመድ ካሣ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ መስተጋብር በበጎ ፍቃደኝነት የተቃኘ መሆኑን ተናግረዋል።   

በጎ ፈቃደኝነት ሰዎች በዘርና በሃይማኖት ሳይታጠሩ የሚገናኙበት ማኅበራዊ መስተጋብር መሆኑንም ነው የተናገሩት።  

የዓለም የበጎ ፈቃድ ቀን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከኅዳር 26 ቀን 1985 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን፤ ቀኑም በዋናነት በጎ ፈቃደኞችን በሚያበረታቱ መርሃ ግብሮች ታስቦ ይውላል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም