በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የደረሰበትን ልህቀት ያማከሉ የዘርፉን ውጤቶች በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ማፋጠን ይገባል

21

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27/2015 በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የደረሰበትን ልህቀት ያማከሉ የዘርፉን ውጤቶች በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ማፋጠን እንደሚገባ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራማሪዋ ዶክተር አበባ ብርሃኔ አመለከቱ።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ማሽኖችን በመጠቀም ሰው ሰራሽ የሆነ የማሰብ ክህሎትን ለተለያዩ የሥራ መስኮች የመጠቀም ቴክኖሎጂ ነው።

ማሽኖች ሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታ እንዲኖራቸው በማድረግ ካለሰዎች እርዳታ ራሳቸውን ችለው ሥራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምንነትና አሁን ባለንበት ዘመን የሚሰጠውን ጠቀሜታ በተመለከተ ኢዜአ በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ደብሊን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራማሪና የኮምፒውተር ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር ከሆኑት ዶክተር አበባ ብርሃኔ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ተመራማሪዋ እንደሚሉት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅ ያሉትን የስሜት ህዋሳት ክህሎቶች ለማሽኖች በማስተማር ሰዎች ነገሮችን በቀላሉ እንዲያገኙና እንዲተገብሩ ማስቻል ነው።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሲባል ከሮቦትና ከግዙፍ ማሽኖች ጋር የማያያዝ የተሳሳተ አመለካከት አለ የሚሉት ዶክተር አበባ በኢንተርኔትና በስልካችን አማካኝነት እንደ ካርታ፣ መረጃና ፎቶ የመሳሰሉት የየቀን ጉዳዮችም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አካል ናቸው ይላሉ።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ እየተስፋፉ ከሚገኙ አገልግሎቶች መካከል ማሽን ትራንስሌት ወይም የቋንቋ ትርጉም አንዱ መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር አበባ በኢትዮጵያም አንዱን ቋንቋ ወደ ሌላ በመተርጎም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እያደገ የመጣውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልህቀት በመመልከት ሀገራችንን የሚመስሉ የዘርፉን ውጤቶች መተግበር አስፈላጊ ነው።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ ልህቀት ዋና ዓላማ የሰዎችን ድካም በማሳጠር አገልግሎት መስጠት ነው፤ በዚህ ረገድ በተለይም በሕክምናና በግብርናው ዘርፍ የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ ነው ይላሉ።

በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግም እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትንም በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዙ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።

በዓለም የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ውስጥ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እያሳደረ የሚገኘውን ተጽዕኖ በመረዳት ተቋማት መገንባትና ለዘርፉ ምርምሮች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ተመራማሪዋ ገልጸዋል።

ዓለም የሚሄድበትን ፍጥነት በመመልከት ሀገራችንን የሚመስሉ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤቶችን ለመተግበር በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም