ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ ልማትን የሚያረጋግጡ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ ልማትን የሚያረጋግጡ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለጸ
አዳማ መስከረም 18/2011 ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ ልማትን የሚያረጋግጡ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታወቀ። በአፋር፣ሶማሌ፣ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የአቅም ክፍተቶችን ለመሙላት ድጋፍ እንደሚደረግ በሚኒስቴሩ የልዩ ድጋፍ ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገነነ አምበሉ ገልጸዋል። በዚህም በሚኒስቴሩና በክልሎች ሁለንተናዊ ልማት እንዲረጋገጡ የአቅም ክፍተቶችን ለመለየትና ክልሎቹ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ለመለየት እየተሰራ ነው። በተለይ ከአመለካከት፣ ከግብዓት፣ ከክህሎት፣ ከክትትልና ግምገማ አንፃር የተለዩ ችግሮችን ለማቃለል ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት መሰጠቱን አቶ ገነነ አመልክተዋል። በዚህም ዘንድሮ ከጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች 36 ባለሙያዎች በመጀመሪያ ዲግሪና በድህረ ምረቃ መርሐ ግብር የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ይደረጋል። ከአራቱም ክልሎች የሚውጣጡ 237 ባለሙያዎች የሙያ ደረጃ በተዘጋጀላቸውና በፀደቀላቸው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ ሥልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል። በከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት ሙያዊ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚደረግ ሲሆን፣ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ዘመናዊ እንዲሆን የዳታ ቤዝና ይዞታ ማህደር አጠቃቀም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አቶ ገነነ አስታውቀዋል። በከተሞች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለሚቋቋሙ ለአረንጓዴ ልማትና ውበት ሥራዎች ትኩረት መስጠቱንና ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን ልማትና ዕድገት የሚያፋጥኑ ተግባራት እንደሚከናወኑ አብራርተዋል። የአፋር ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ግምገማ ከፍተኛ ኦፊሰር አቶ አብዱልከሪም ሲራጅ በሰጡት አስተያየት ከሚኒስቴሩ ጋር የተቀናጀ ዕቅድ በማዘጋጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በተቀናጀ የከተሞች መሰረተ-ልማት አቅርቦት፣ በሥራ እድል ፈጠራ፣ በቤቶች ልማት፣ በከተማ ፕላን አዘገጃጀትና አተገባበር፣ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ በአቅም ግንባታና በሌሎችም መስኮች ተቀራርበን እየሰራን ነው ብለዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት ባለሙያ አቶ ሐብታሙ ገመዳ በበኩላቸው ከሚኒስቴሩ ጋር የተዘጋጀው ዕቅድ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች የነደፏቸው ዕቅዶች እንዲያሳኩና በክልሎች መካከል የሚታየውን የዕድገት አለመመጣጠን ክፍተት ለማጥበብ እንደሚረዳ ተናግረዋል። የአጎራባች ክልል ህዝቦችን የቆየ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የአኗኗርና የባህል ትስስር በማሳደግና በመጠበቅ በልማትም ሆነ በዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታው ተቀናጅተውና ተደጋግፈው እንደ ክልል የሚደረግላቸውን ድጋፍ ለመጠቀም እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።