የበለፀገችና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት መንግስት ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የበለፀገችና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት መንግስት ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 የበለፀገችና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መንግስት ከምሁራን ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
የተሻለች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደትም ምሁራን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
'ለኢትዮጵያ ልዕልና የምሁራን ሚና' በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የምሁራን የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲሁም ሰላምና መረጋጋት የምሁራን አበርክቶ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በምክክሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ያሉባትን ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግሮች ከመፍታት አኳያ በተለይም ምሁራን ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ተቋም አለመገንባታችን፣ የአንድነት አስትሳሰብን በሚያላሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮራችን፣ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ መግባታችን የኢትዮጵያን ችግር ውስብስብ እንዳደረገው ጠቅሰዋል።
ሌብነት በሰፊው መንሰራፋቱ፣ ግለሰቦች ተቋም የሆኑበትና ፖለቲካን እንደሸቀጥ የመገልገል አዝማሚያም ሀገሪቱን የከፋ ችግር ውስጥ ከቷት እንደቆየ አንስተዋል።
ኢትዮጵያን ከበለጸጉት ሀገራት ተርታ ማሰለፍ የሚችል ወጣት፣ ሰፊ መሬትና እምቅ አቅም ቢኖርም እስከዛሬ በአግባቡ አልተጠቀምንበትም ብለዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ እድገትና ተደራሽነት፣ ማህበራዊ መሠረት፣ አርቆ አሳቢ ትውልድ፣ እንዲሁም ቋሚ ሀብት መገንባት የግድ እንደሆነ አመላክተዋል።
መንግስት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማሳካት ሲነሳ ሀገር በሚገነቡ በምሁራን የጥናትና ምርምር ሀሳቦች በመተማመን መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ስረ-መሰረታዊ ችግር ለመንቀል፣ እምቅ አቅሟን ጥቅም ላይ ለማዋል ምህራን በጥናትና ምርምር ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ እምቅ የመልማት እቅም ቢኖራትም ከልመና አለመላቀቋን አንስተው፤ መንግስት የኢትዮጵያን መጥፎ ገጽታ የሚቀይሩ አጠቃላይ የማህብራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ መግባቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም መንግስት የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከምሁራን ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ቀጣዩ አገር ተረካቢ ተውልድ ልመና የማይወርስባት የበለጸገችና ከፍታዋ እውን የሆነች አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ምሁራን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
መንግስት ከፖለቲካ ሪፎርም እስከ ተቋማዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ይህ እንዲሳካ ጥልቁን የኢትዮጵያ ችግር በምርምርና በምክክር መፍታት አለብን ነው ያሉት።
በዚህ ጥረት ውስጥ ምሁራን የፖለቲካ ብልሽቱን በመቀየር ሁሉም ፍትሀዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ በማፈላለግ መንግስትን ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
ለዚህም ከመንደር አስተሳሰብ መውጣትና ለሁሉም የምትመች የበለፀገች ኢትዮጵያን በመገንባት ለትወልድ እናስረክብ ብለዋል።