ቀጥታ፡

በየጊዜው እየረቀቀ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል ዘመኑን የዋጀ የመከላከል ስልት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በየጊዜው እየረቀቀና እየተወሳሰበ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል ዘመኑን የዋጀ የመከላከል ስልት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ የስነ-ምግባርና ሙስና መከላከል ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም እየረቀቀና እየተወሳሰበ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል ዘመኑን የዋጀ የመከላከል ስልት አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት እየሆነ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል አስፈላጊው ሁሉ ጥረት ሊደረግ ይገባል ሲሉም ጠቅሰዋል።

ረቂቅ ሰነዱን በማስመልከት ለተሳታፊዎች ገለጻ ያደረጉት በስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና አስፈጻሚዎች ማስተባባሪያ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሃረጎት አብርሃ፤ ከዚህ ቀደም በአገር ደረጃ የጸረ ሙስና ትግሉ የሚመራበት ወጥ ሰነድ አልነበረም ብለዋል።

በ2013 ዓ.ም ኮሚሽኑ ባደረገው ጥናት መሰረት ሙስና ብሔራዊ ስጋት መሆኑን ማመላከቱን አስታወስው አደጋውን ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶችን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ የሚመጥን ምላሽ ለመስጠትና መንግስት እያደረገ የሚገኘውን ትግል ለማጠናከር ረቂቅ ፖሊሲውን ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የአገር ስጋት የሆነውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት የፖሊሲው መዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በይዘት በጥሩነት የተነሱት እንዳሉ ሆነው መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ጠቅሰው በቀጣይ በፖሊሲው ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፤ ፖሊሲው የሙስና ወንጀል የብሔራዊ አደጋ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡

በፀረ ሙስና ትግሉ በመንግስት ጠንካራ አቋም መያዙን ገልጸው ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የህዝቡ እገዛ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ የሚዲያ ሃላፊዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች፣ የጥበብ ሰዎች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም