ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ህንድ ሄደው ለሚታከሙ 100 የልብ ህሙማን ህጻናት የትራንስፖርት ወጪያቸውን ሸፈነ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ህንድ ሄደው ለሚታከሙ 100 የልብ ህሙማን ህጻናት የደርሶ መልስ ሙሉ የትራንስፖርት ወጪያቸውን ሸፈነ።

አየር መንገዱ በሮተሪ ኢንተርናሽናል የህክምና ወጪያቸው ተሸፍኖ ወደ ህንድ ሄደው ለሚታከሙ የልብ ህሙማን ህፃናት የደርሶ መልስ ሙሉ የትራንስፖርት ወጪያቸውን መሸፈኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ፤ አየር መንገዱ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ለህዝብ የሚያደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትሯ አማካሪ ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል፤ በኢትዮጵያ ከልብ ህመም ጋር የሚወለዱ ህፃናትና ካደጉም በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠር ህመም በርካታ ህፃናት ለልብ ህመም ችግር እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የልብ ታማሚ ህፃናትን ችግር ለማቃለል ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ፣ ህንዳዊው የሮተሪ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ፕሬዚዳንት፣ በበጎ አድራጎት እየሰራ የሚገኘውን የህጻናቱን የልብ ህክምና እውን ለማድረግ የተባበሩትን ባለድርሻ አካላት አመስግነዋል።

በኢትዮጵያ የሮተሪ ኢንተርናሽናል የበጎ አድራጎት የኢትዮጵያ ተወካይ ተሾመ ከበደ፤ ህንዳዊው የሮተሪ ፕሬዚዳንት ከአንድ አመት በፊት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የህጻናቱን ችግር አይተው መሄዳቸውን አንስተዋል።

አሁን ላይ ለ100 ህጻናት ይህ እድል እንዲሰጥ በማድረግ ህጻናቱ ወደ ህንድ ሄደው እንዲታከሙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ፕሬዚዳንት ሳላሃዲን ከሊፋ፤ ማዕከሉ የህጻናቱን ችግር ለማቃለል እየሰራ ቢሆንም ህክምና ለማግኘት በርካታ ህጻናት አሁንም ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው ብለዋል።

ማእከሉ በየአመቱ በአማካይ ለ600 ህጻናት የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በማንሳት ከህክምና ፈላጊዎች አንፃር ተደራሽ ለመሆን ብዙ መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም