ግሩፑ በ750 ሚሊዮን ብር ካፒታል በግብርና፣ በማዕድንና ውሀ ልማት ዘርፍ መሰማራቱን አስታወቀ

126

አሶሳ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ750 ሚሊዮን ብር ካፒታል በግብርና፣ በማዕድንና ውሀ ልማት ዘርፍ መሰማራቱን የቤጉ ዴቨሎፕመንት ግሩፕ አስታወቀ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት “የቤጉ ዴቨሎፕመንት ግሩፕ” (BG Development Group) የተሰኘ የመንግስት የልማት ድርጅት እንዲቋቋም ውሳኔ ማሳለፉን ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል።

የግሩፑ ዓላማ  ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ እንዲለማ ማድረግ መሆኑን የዴቨሎፕመንት ግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ቴሶ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ሃገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር ማገዝም ሌላው ዓላማ መሆኑን አመልክተዋል።

"ህብረተሰቡን ከተፈጥሮ ሀብቱ በበለጠ ተጠቃሚ ማድረግ ከድህነት እንዲወጣ ያስችላል፤ ከዚህ ባሻገር ሃብቱ ለሃገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያደርጋል" ብለዋል።

ግሩፑ የኢንቨስትመንትና የንግድ አዋጁን እንዲሁም በነጻ ገበያ ህግ መሠረት በዘርፉ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስራ በቅርቡ መጀመሩን ገልጸዋል።

መሠረተ ልማትን ጨምሮ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ገቢን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

ፍትሃዊ ውድድርን መሠረት በማድረግ  የሚንቀሳቀሰው ግሩፑ፤ በማዕድን፣ በሰፋፊ እርሻ፣ በውሃ ስራዎችና በኢንቨስትመንት ዘርፎች እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በቱሪዝምና በተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበር ጨምሮ የተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ደግሞ በቀጣይ የሚሳተፍባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደሚሆኑ አቶ መንግስቱ ጠቁመዋል።

በረጅም ጊዜ የህብረተሰቡን የምግብ ፍጆታ ለመሙላት በገበያ እጥረት የሚታይባቸው የእህል ዘርፎች ላይም እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

ግሩፑ በኢንቨስትመንቱ የተሰማራው 750 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ እንደሆነ ተናግረዋል።

ግሩፑ በቅርቡ በሙከራ ደረጃ በክልሉ ባምባሲ ወረዳ ሰላማዳቡስ ቀበሌ በ46 ሄክታር መሬት ላይ በጀመረው የአኩሪ አተር ልማት ብቻ 100 ለሚጠጉ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

"ግሩፑ የኢንቨስትመንት ስራውን ከሙስና በጸዳ መልኩ ያካሂዳል" ሲሉም አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ በተለይም ባለሃብቱና ባለድርሻ አካላት ከግሩፑ ጋር በመተባበር ለድህነት ቅነሳው የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ዋና ስራ አስፈጻሚው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም