በቀጠናው ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የፖሊስ ተቋማት በቅንጅት መስራት አለባቸው -ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
በቀጠናው ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የፖሊስ ተቋማት በቅንጅት መስራት አለባቸው -ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 26 /2015 በቀጠናው ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የአገራት የፖሊስ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተናገሩ።
ከትናንት ጀምሮ በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ሕብረት ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።
በመድረኩም ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የፀረ ሽብርተኝነት ትግል ተሞክሯቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵየ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትን ጨምሮ የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች እየተበራከቱ መሆኑን ገልጸዋል።
የአደገኛ እጽና ሕገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር መበራከት፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች የቀጣናው ፈተና ሆነዋል ነው ያሉት።
እነዚህ ወንጀሎች ለቀጣናው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች መበራከት ሳንካ ሆነው ቀጥለዋልም ነው ያሉት።
በመሆኑም የወንጀል ተግባራቱን ለመከላከል የአገራቱ የፖሊስ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል ኮሚሽነር ጀነራሉ።
ኢትዮጵያ በፀረ-ሽብር ትግል ውጤታማ ልምዶች እንዳሏት የጠቀሱት ኮሚሸነር ጄነራሉ፤ የፖሊስ ተቋምን ለመገንባትና ብቁ መኮንኖችን ለማፍራት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመመከት ለቀጣናው ሰላም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጸጋዬ ሃይሉ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ሕብረት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ሽብርተኝነትን ከመከላከል አኳያ ያላትን ምርጥ ተሞክሮ ማጋራቷን ገልጸዋል።
ሌሎች አገራትም በድንበር ዘለል ወንጀሎች ላይ ያላችውን ልምድና ተሞክሮ አቅርበው ምክክር እንደተደረገበት ገልጸዋል።
አገራት በሕግ ማስከበር ረገድ ያላቸውን የተሻለ ተሞክሮ እንዲያጋሩ፣ ከሌሎችም ልምድ እንዲቀስሙ ብሎም ተቋማት ተቀራርበው እንዲሰሩ በማድረግና አቅምን በመገንባት ረገድ ስብሰባው ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል ኮማንደር ጸጋዬ።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ጠቅላላ ጉባኤ እስከ ሕዳር 30 ቀን 2015 ይቆያል።