የኤሌክትሪክ ኃይል-አንድም ብርሀን አንድም ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ

የኤሌክትሪክ ይል

አንድም ብርሀን አንድም ቀጣናዊ ትስስር መፍጠሪያ መሳሪያ

(በሰለሞን ተሰራ)

የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት የሚስተዋልበት በመሆኑ በአካባቢው በሚገኙ አገራት መካከል ጠንካራና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለመመስረት አዳጋች ሆኖ ቆይቷል። አካባቢው ለዘመናት የዘለቀ አለመረጋጋት የሰፈነበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ደካማ የሆነ የፖለቲካ አብሮነት ሲንጻባረቅበት የቆየ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይስማሙበታል።

ቀጣናው ከኢኮኖሚ ትብብር ይልቅ ወታደራዊ ትብብር የሚጎላበት፣ የአንድን አገር የውስጥ ሰላም ለማደፍረስ የተለያዩ አገራት ረጃጅም እጆቻቸውን የሚዘረጉበት፣ አገራት በጎረቤቶቻቸው ላይ ሴራ የሚጠነስሱበት እንደነበርም በቻታም ሀውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ተባባሪ ተመራማሪና የጥናት ተንታኝ የሆኑት ሳሊ ሄሊ የተባሉ የፖለቲካ ምሁር ይጠቅሳሉ።

በዚህም በቀጣናው የሚስተዋለው የእርስ በርስ ግጭት፣ አለመረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገት ከማጓተቱ ባለፈ አገራቱ እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ አድርጓቸው ቆይቷል።

ሳሊ ሄሊ እንደሚሉት በአገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ተመሳሳይ ማህበረሰቦች በርካታ በመሆናቸው በአንዱ አገር የሚፈጠረው የደህንነት ስጋት ሌላኛውን በቀጥታ ይጎዳዋል። ማህበረሰቦቹ አንድ አይነት የአኗኗር ባህል የተላበሱ በመሆኑ የመኖር ህልውናቸውም ሆነ ብልጽግናቸው ተነጣጥሎ የሚታይ አይደለም።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ከሚገኙ ሁሉም አገራት ጋር ድንበር የምትጋራ በመሆኑ የስጋቱ ቀጥተኛ ተጠቂ ናት። ይህን ተከትሎ ስጋቱን ወደ መልካም ዕድል ለመቀየር የተለያዩ የዲፕሎማሲ መስመሮችን በመዘርጋት የቀጣናውን ትስስር ጠንካራና ዘላቂ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች።

በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠርና የአፍሪካ ሕብረት ለአህጉሪቱ ልማት፣ ሰላምና ውህደት መሳሪያ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዲጠናከር ለማስቻል በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል።

ኢትዮጵያ በ”ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ” ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖርና የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በመትጋትም አርአያነቷን እያሳየች ትገኛለች።

ከጎረቤቶቿ ጋር በወደብ፣ በባቡርና በየብስ ትራንስፖርት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብቱ አያሌ መሠረተ ልማቶች ከመተሳሰር ባለፈ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የምታደርገው ጥረት በአርአያነት እንድትጠቀስ አድርጓታል።

ነገር ግን ከአፍሪካ ቀንድና ከጎረቤት አገራት ጋር ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ያልተዋጠላቸውና የቀጣናው መረጋጋት ጥቅማችንን ያሳጣናል ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ኃያላን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር አገሪቱ ከያዛቸው ግብ ወደ ኋላ ለመሳብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ በግልጽ ይስተዋላል።

ጫናዎቹ እንዳሉ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ከትብብርና አብሮ መልማት አካሄዷ ዝንፍ አላለችም። ቀጣናውን በኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት ለማስተሳሰር የወጠነችውን ግብ ለማሳካት ያግዛት ዘንድ ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የጀመረችውን ጥረት ገፍታበታለች።

ለአብነትም የውሃ፣ ነፋስ፣ እንፋሎትና የጸሃይ ብርሃን በመጠቀም ኃይል አምራች በመሆን ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር የአፍሪካ የኃይል ምንጭ ማዕከል ለመሆን ግብ ጥላ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። 

የኃይል አቅርቦት ጅማሮው በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ድንበር ዘለል የሃይል ንግድ እንዲሁም ትስስርን ለማጎልበት ያግዛል። ይህም በአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጣር 2005 የተቋቋመው ኢስተርን አፍሪካ ፓወር ፑል እንቅስቃሴ ተግባራዊነት የሚያረጋግጥ ነው።

ኢስተርን አፍሪካ ፓወር ፑል ምስራቅ አፍሪካን በአስተማማኝና ዘመናዊ የኃይል አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በዓለም ላይ ካሉ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዱ ተብሎ ወደሚታወቅ ቀጣና የመቀየር ራዕይ አለው።

በአጠቃላይ የኃይል ልማትን የማስተባበር ስልጣን የተሰጠው የተቋሙ ዋና ፅህፈት ቤት በአዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን አስራ አንድ አባል አገራት አሉት። አገራቱም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሊቢያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ናቸው።

ይህን የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ፖል ኢኒሸቲቭን መሰረት አድርጋ የምትንቀሳቀሰው ኢትዮጵያ በቀጣናው ለሚገኙ በርካታ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

አሁን ላይ ለኬኒያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ ኃይል የምታቀርብ ሲሆን በቀጣይ ለታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን ኃይል በማቅረብ ምስራቅ አፍሪካን በልማት ለማስተሳሰር እየተጋች ነው፡፡ በቀጣይ ዓመታትም የኃይል ምርትና የአቅርቦት ምጣኔዋን በማሳደግ የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የኃይል አቅራቢ ለመሆን እየሰራች ነው።

ኢትዮጵያ ለጂቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል የምትሸጥበት ታሪፍ ተቀራራቢነት ያለው ሲሆን በዋናነት የጋራ የልማት ትስስርን መሰረት ያደረገ ነው። በ2014 ዓ.ም. ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለጅቡቲ 527 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማቅረብ ታቅዶ 611 ጊጋ ዋት ሰዓት ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ለሱዳን ደግሞ 1 ሺሕ 93 ጊጋ ዋት ሰዓት ማቅረብ መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

መንግስት ለጅቡቲና ሱዳን ካቀረበው የኃይል ሽያጭ ያገኘው 95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን፤ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም የ5 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እንዳለውና የአገራቱ ትስስር እየጎለበተ መምጣቱን ያሳያል። አገራቱ ካለባቸው የኃይል እጥረት አኳያ የኢትዮጵያ በጋራ የመልማት አካሄድ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ይገኛል። በተለይ ጅቡቲ ኃይል ለማመንጨት ለድንጋይ ከሰልና ለነዳጅ የምታወጣውን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ከስምምነቱ በእጅጉ ተጠቃሚ ያደርጋታል።

ሱዳን ከዚህ ቀደም ወደ 200 ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ እንደገዛችና ይህም የሱዳንን 10 በመቶ የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎትን እንደሚሸፍን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያና ኬንያ በኃይል ለመተሳሰር የጀመሩት ጉዞ በቅርቡ ለፍሬ በቅቷል። በ2008 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው የኢትዮ-ኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ 1 ሺ 068 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን፣ አጠቃላይ ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 26 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶበታል። የማስተላለፊያ መስመሩ በኢትዮጵያ በኩል 437 ኪ.ሜ በኬኒያ በኩል ደግሞ 631 ኪ.ሜ. ርዝመት አለው።

በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው መስመር ከወላይታ-ሶዶ ማከፋፈያ ጣቢያ ጀምሮ አርባ ምንጭ፣ ኮንሶ፣ ብርንዳር፣ ያቤሎና ሜጋንን አቋርጦ ኬንያ የሚዘለቅ ሲሆን ግንባታው በመጠናቀቁ ኢትዮጵያ ለኬኒያ ኃይል ማቅረብ ጀምራለች። ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት ለሩዋንዳ፣ ለታንዛኒያና ለብሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ውይይት የጀመረች በመሆኑ የኬንያው መስመር ዝርጋታ ለኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

አዲስ የተገነቡትና በመገንባት ላይ የሚገኙት እንደ ግልገል ጊቤ 3፣ ኮይሻና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬቱን ለማፋጠን አጋዥ ተደርገው ይቆጠራሉ።

የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ቀጣናውን በኃይል ከማስተሳሰር ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ስጋት የሆነውን የአየር ፀባይ ለውጥ ለመከላከል የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ወደ ጎረቤት አገር የሚላኩት የኤሌክትሪክ ኃይልና የወጭ ንግድ ምርቶች ኢትዮጵያ በኢጋድ አገሮች ውስጥ ለሚኖረው አካባቢያዊ ትስስር የሰጠችውን ከፍተኛ ትኩረት ያመለክታል።

በዚህም ከኃይል አቅርቦቱ ባለፈ በኢትዮጵያ በኩል አልፈው ወደ ኬንያ፣ ሶማሌላንድ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ የሚዘልቁ ከ13 በላይ የመገናኛ ኮሪደሮች ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ረገድ የምታደርገውን እንቅስቃሴ በሚያግዝ አግባብ ሰፊ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ላይ ትገኛለች። በመንገድ፣ በባቡር፣ በነጻ የንግድ ቀጣና፣ በኃይል ትስስር እየሰራቻቸው ያሉ ስራዎች በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።

አገሪቷን በአገር ውስጥና በክፍለ አህጉሩ ደረጃ ለማገናኘት የሚያግዝ 4 ሺ 744 ኪሎ ሜትር የሃዲድ መስመር የሚሸፍን ስምንት የባቡር መንገድ ኮሪደሮች በሁለት ምዕራፍ ለመገንባት የተያዘው ዕቅድ ሌላው ማሳያ ተደርጎ ሊነሳ ይችላል።

የኢትዮጵያ የገቢ ሸቀጥ 90 በመቶ በጅቡቲ ስለሚገባ የኃይል አቅርቦቱ ይህንኑ የወደብ እንቅስቃሴ ለማሳለጥና የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊና የአገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለው ሚና ወሳኝ ነው።

ቀጣናው በአየር ጸባይ ለውጥ የተነሳ ለተደጋጋሚ ረሃብ፣ ድርቅ፣ ጎርፍና የአንበጣ ወረረርሽኝ የተጋለጠ በመሆኑ የታዳሽ ኃይል ግንባታ ጥረቱ በመጠንም ቢሆን እነዚህን ስጋቶች እንደሚያስወግድ ታምኖበታል።

ኢትዮጵያ ለአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያት ባትሆንም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ ግንባር ቀደም የምስራቅ አፍሪካ አገራት አንዷ ናት። የታዳሽ ኃይል አቅርቦቱ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የስራ ዕድል በመፍጠር፣ ከባቢያዊ ሁኔታን በመጠበቅና የደን ሃብትን ከውድመት በመታደግ የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ከዚህ ባለፈ ትስስሩ የአገራቱ የፖለቲካና የለውጥ መሰረት ለሆነው አገር ተረካቢ ወጣት ዘርፈ ብዙ የስራ ዕድል በመፍጠር ትውልዱን ከስጋት ምንጭነት ወደ ልማት ፊት አውራሪነት ለመቀየር ያስችላል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢነርጂ ማዕከል ለመሆን በያዘችው እቅድ የውሃ፣ የነፋስ፣ የእንፋሎት እና የጸሃይ ብርሃን ሀይል የማመንጨት አቅሟን ለማሳደግ እየሰራች ትገኛለች። ይህም ንጹህ ኢነርጂን በመጠቀም ረገድ በዓለም ላይ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥን የሚያሳይ እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ንጹህ ኢነርጂን በመጠቀም ቀዳሚ እንድትሆን እንደሚያስችላት ተገልጿል። ይህም ከቀጣናው ባለፈ አፍሪካን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር የጀመረችውን ቁርጠኛ አካሄድ ያረጋግጣል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ2013-2022 የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ እንደተመላከተው በአገር ውስጥ ያለውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርቶችን የሚያሟላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለጎረቤት አገራት ማቅረብን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ይህም ኢትዮጵያ ጎረቤትን ያስቀደመ በጋራ የመልማት አካሄዷ ማሳያ ብቻ ሳይሆን ማረጋገጫ መሆኑን ከልማት ዕቅዱ ተጨልፈው በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑና ለውጤት የበቁ የልማት ስራዎች ምስክሮች ናቸው።

እነዚህን ትስስሮች በማጎልበት መተማመንን የሚፈጥሩ ተግባራት ማጠናከርና በጋራ በመልማት መርህ ላይ ተመስርቶ መስራት የሁሉም አገራት ቀዳሚ አማራጭ ሊሆን ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም