የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ

81

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ እና እድል ተጠቅመው መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ።

አምባሳደሩ በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው የኢንቨስትመንት ሴሚናር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው ጥሪውን ያቀረቡት።

በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ለማጎልበት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሴሚናሩ ላይ ለተሳተፉ የጃፓን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስላሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ህጎች፣ምቹ ሁኔታዎች፣አስቻይ የኢኮኖሚ ከባቢ እንዲሁም የኢንቨስትመንት መስረተ-ልማቶች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።


በተጨማሪም፤ አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ጨርቃጨርቅ፣መድሃኒት፣ማዕድንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች በኢንቨስትመንት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በሴሚናሩ ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንት አማራጭ ጠቃሚ መረጃ ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።


በጃፓን በሃይል፣ኮንስትራክሽን፣አግሮ ፕሮሰሲንግና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ 13 ኩባንያዎች በሴሚናሩ ላይ መሳተፋቸውን በጃፓን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም