በቡና ምርት ልማትና ጥራት ላይ ያተኮረ የቡና አምራች አገራት የልምድ ልውውጥ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ምርት ልማትና ጥራት ላይ ያተኮረ የቡና አምራች አገራት የልምድ ልውውጥ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 26/2015 በቡና ምርት ልማትና ጥራት ላይ ያተኮረ የቡና አምራች አገራት የልምድ ልውውጥ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በልምድ ልውውጡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የኮሎምቢያ፣ ስፔን፣ ሆንዱራስና የሌሎች አገራት የዘርፉ አምራቾችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ከዛሬ ጀምሮ እስከ የፊታችን ቅዳሜ ድረስ በሚካሄደው የቡና ምርት ልማትና ጥራት ላይ ያተኮረው የቡና አምራች አገራት የልምድ ልውውጥ ለጋራ ልማትና ተጠቃሚነት የሚያግዙ ግብዓቶች እንደሚገኙበት ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የቡና ምርታማነትና ጥራት ከፍተኛ ለውጥና ውጤት እየተገኘበት ነው።
በ2014 በጀት ዓመት ከቡና ምርት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮም በገቢና በምርት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ልማት የያዘችውን ዕቅድ እንድታሳካ ደግሞ ከአምራች አገሮች ጋር የሚደረገው የተሞክሮ ልውውጥ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በአንዳንድ አገራት በሄክታር እስከ 20 ኩንታል የሚገኝበትን የቡና ምርት በኢትዮጵያም ማግኘት የሚያስችል ተሞክሮ እንጋራበታለን ብለዋል።
የልምድ ልውውጡ በበጀት ዓመቱ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ በማሳካት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረውም እንዲሁ፡፡
በኢትዮጵያ አሁን እየተገኘ ያለውን በሄክታር የሰባት ኩንታል ምርት ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የልምድ ልውውጡ ተሳታፊ ከሆኑት ባለሙያዎች መካከል ስፔናዊው ማሪዮ ፋንጁል፤ ኢትዮጵያ በቡና ምርት ልማት እምቅ አቅም ያላት አገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በጋራ ለማደግ የልምድ ልውውጡ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የቡና ምርት ልማትን ማዘመን ከተቻለ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የልምድ ልውውጡ እስከ የፊታችን ቅዳሜ የሚቀጥል ሲሆን በኢትዮጵያ የቡና ምርት ልማት በሚከናወንባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ጉብኝት የሚደረግ ይሆናል።