ቀጥታ፡

ደኢህዴን ለውጡን የሚያስቀጥሉ አመራሮች ወደኃላፊነት እንዲያመጣ ተጠየቀ

አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የተጀመረውን ለውጥ የሚያስቀጥሉ አመራሮችን ወደኃላፊነት ማምጣት እንዳለበት ተገለፀ። ይህ የተገለፀው የንቅናቄው 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ሲጀመር የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና አጋር የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስተላለፉት መልዕክት ነው። እህት ድርጅቶቹና አጋር ፓርቲዎቹ በተወካዮቻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ጉባኤተኛው የክልሉን ህዝቦች ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉና አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ወሳኔዎችን ያሳልፋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ተወካይ አቶ በፍቃዱ ተሰማ በኢትዮጵያ የነበረው የጥላቻና የሰዶ ማሳደድ አካሄድ ተመልሶ እንዳይመጣ የለወጡን ሂደት ከእሾህ ማጽዳት እንደሚገባ ጠቅሰው ለውጡን ለማደናቀፍ የሚያስቡ አካላትን በፍቅርና በአንድነት ኃይል ማሸነፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ደኢህዴን ላለፉት ዓመታት ያካሄደውን ትግልና መስዋዕትነት መገለጫው የሆነውን ብዝሀነትና አንድነት ባስጠበቀ መልኩ ወደፊትም መቀጠል እንዳለበት የኦዴፓ ተወካይ ተናግረዋል። የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ተወካይ ተወልደ ገብረጻድቃን በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት በደቡብ ክልል የታዩት ችግሮች ከለውጡ ጋር ተያይዘው የመጡ መሆናቸውን ጠቁመው ደኢህዴን እነዚህን ችግሮች በተለመደው የውስጥ ትግል ሊፈታቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ነው ያሉትን የህገ-መንግስት ጥሰት በጋራ ለመከላከል ደኢህዴን የበኩሉን እንዲያደርግ የህወሃቱ ተወካይ ጥሪ አቅርበዋል። "ደኢህዴን የፌዴራል ስርዓቱን ለመጠበቅ ያደረገውን ጥረት ህወሃት በከፍተኛ ደረጃ ያደንቃል" ሲሉም ገልፀዋል። የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ተወካይ አቶ ባዘዘው ጫኔ ባስተላለፉት መልዕክት ደግሞ ደኢህዴን የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ውሳኔ በጉባኤው እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል። የደቡብ ክልልንና እና የአማራ ህዝቦችን ግንኙነት ለማበላሸት ለዓመታት የተካሄደው ሴራ አለመሳካቱን ተወካዩ ጠቅሰዋል። ደኢህዴን የሚያካሄደው ጉባኤ የክልሉን የብዝሀነትና ተከባብሮ የመኖር ፀጋ የሚያጎላ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋም ገልፀዋል። በጉባኤው የሚተላለፉትን ውሳኔዎች በመቀበል ለተፈፃሚነታቸው ብርቱ ጥረት እንደሚያደርጉ የሶስቱም እህት ድርጅቶች በተወካዮቻቸው በኩል አረጋግጠዋል። የኢህአዴግ አጋር የሆኑት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉዴፓ)፣ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ)፣ የሀረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሀብሊ) እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) ተወካዮች መልዕክትም በጉባኤው ላይ ተደምጧል። አጋር ፓርቲዎቹ በዚሁ መልዕክታቸው ደኢህዴን ወደህዝቡ የበለጠ በመቅረብ ለለውጥና ለአንድነት የሚበጁ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል። ጉባኤው ዘረኝነትን ለማስፋፋትና ለውጡን ለማሰናከል የሚሞክሩ የአመራር አካላትን በመለየት የለውጥ አራማጅ መሪዎችን ይሰይማል የሚል  እምነት እንዳላቸውም አጋር ድርጅቶቹ ገልፀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም