ሀገርን ከብሔራዊ አደጋ ስጋትና ከዘረፋ ለመታደግ የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል- አቶ ተስፋዬ በልጂጌ

23

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 26/2015 ሀገርን ከብሔራዊ አደጋ ስጋትና ከሃብት ዘረፋ ለመታደግ በመንግስት የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ ተናገሩ።

የመንግስት የጸረ ሙስና ትግል የሀገርን ህልውና የማስጠበቅና ሌብነትን መዋጋት በመሆኑ የዜጎች ትብብርና ጥረት እንዲታከልበትም ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተንሰራፋ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የፀረ ሙስና ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን የጀመረ ሲሆን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችና የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፤ መንግስት የጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ሀገርን ከዘረፋ የማዳንና ብሔራዊ ደህንነቷን የማረጋገጥ የህልውና ትግል መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገርን ከብሔራዊ አደጋ ስጋትና ከዘረፋ ለመታደግ በመንግስት የተጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በመንግስት ጥረት ብቻ የሙስና ትግል የሚሳካ ባለመሆኑ አጠቃላይ የዜጎችን ቀና ትብብርና የመከላከል ጥረት እንደሚያስፈልግም ገልጸው የዜጎች ሁለንተናዊ ትብብርና ያላሰለሰ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የፀረ ሙስና ትግሉን በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማትና የመገናኛ ብዙሃን እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

መንግሥት በየደረጃው የሚገኘውን መዋቅር በመፈተሽ፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን እያሳለጠ ስለመሆኑም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ አመራሮችንና ሌሎች ተዋንያንን ለሕግ ማቅረብ፣ ለሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚከናወነው ተግባር ይቀጥላል ብለዋል።

የመንግስትን የጸረ ሙስና ትግል የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ሰባት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ  ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም