ባለፉት አራት ወራት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 526 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አራት ወራት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 526 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 ባለፉት አራት ወራት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 526 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ኮሎምቢያና ስፔንን ጨምሮ ከተለያዩ ቡና አምራች አገራት ባለሙያዎች ጋር በአዲስ አበባ እየመከረ ይገኛል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በመድረኩ የበጀት ዓመቱን አራት ወራት የኢትዮጵያን የቡና ምርት ግብይት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
ባለስልጣኑ በበጀት ዓመቱ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውሰው ባለፉት አራት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት 526 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት 810 ሺህ ቶን የቡና ምርትን ወደ ውጭ በመላክ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመው የእስካሁኑ እንቅስቃሴ አበረታች ነው ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የአራት ወራት አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ126 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለውም አስታውቀዋል።