ቀጥታ፡

የእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ ላይ ያተኮረ የጥናት ምርምር ውጤት ይፋ ሊሆን ነው

አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 የእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ ላይ ያተኮረ የጥናት ምርምር ውጤት ይፋ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር አስታወቀ፡፡ ማህበሩ ጥናቱን አስመልክቶ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ስብሰባ ያካሄዳል፡፡ በማህበሩ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ዳንኤል ሽታዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ጥናቱ በጤና ተቋማት ያለው የጤና ክብካቤ ጥራት ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም በዚሁ ይፋ በሚሆነው የጥናት ውጤት ላይ ውይይት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ በውይይቱም ላይ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጨምሮ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የማህበሩ አባላት፣ ባለድርሻ አካላት ኃላፊዎች፣  የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተወካዮች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ማህበሩ በኢትዮጵያ በተለይም የእናቶች ቅደመ ወሊድ፣ የወሊድ፣ የድህረ ወሊድ፣ የቤተሰብ እቅድና የተለያዩ አገልግሎቶችን ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች በመስጠት የእናቶችንና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ የቻለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በበጐ አድራጐት ድርጅቶች ማህበራት ኤጀንሲ የተመዘገበ ብቸኛ የሚድዋይፎች ወኪል ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ ከተቋቋመ 27 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በመላው አገሪቱ በሚገኙ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከ5ሺህ በላይ አባላት አሉት፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም