ቀጥታ፡

የስነ-ምግባርና የሙስና ወንጀል መከላከል ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በኢትዮጵያ የስነ-ምግባርና ሙስና ወንጀል መከላከል ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደተነሳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስጋት የሆነው የሙስና ወንጀልን ለመከላከል አስፈላጊው ሁሉ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ተገልጿል።

ለዚህም ኮሚሽኑ ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት ላይ ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ስራ መግባት ያስፈልጋል ነው የተባለው።

ከፖሊሲው ዓላማዎች መካከል ሃላፊነትን መወጣት የሚያስችል አቅምን ማጠናከር እና ተቋማዊ ትብብርና ቅንጅትን ማረጋገጥ መሆኑ ተጠቅሷል።

በፖሊሲው የመንግስት ግዢ፣ መሬት አስተዳደር፣ ትላልቅ የመንግስት ፕሮጀክቶች፣ ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር፣ የገቢ አሰባሰብ አስተዳደር፣ የጉሙሩክ አሰራር፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የፖሊስና የትራፊክ ፖሊስ አሰራር፣ የፍርድ ቤቶች አሰራር፣ የመንግስታዊ የልማት ድርጅቶች አሰራር እና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም /ማዕድን ልማት/ በአገራችን ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች መሆናቸው በረቂቅ ፖሊሲው ተመላክቷል።

ፖሊሲው የተለያዩ መርሆዎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ፣ ስነ ምግባራዊ አሰራር፣ የአሰራር ነጻነት እና ሙያዊ ብቃትን ማሳደግ ተጠቃሽ ናቸው።

የፖሊሲው ስራ ላይ መዋል የጸረ ሙስና ትግሉን ለማሳለጥ እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

በውይይት መድረኩ የሚዲያ ሃላፊዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች፣ የጥበብ ሰዎች እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም