ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ዘላቂነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ  መስከረም 18/2011 ለኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ዘላቂነት የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ በአስመራ የደመራ በዓልን ሲያከብሩ ያገኘናቸው የኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ተናገሩ። ለዘመናት ተቀብሮ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተደበቀበት ይወጣ ዘንድ በአማናዊ ደመራ-ሰማያዊ ምልክት የታየበት ቀን በኤርትራ በዓት መስከረም አደባባይ በድምቀት ተከብሯል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለፁት፤ የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያና ኤርትራ በፍቅር ተደምረው በጋራ ያከበሩበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል። በሁለቱ አገራት መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ የአገራቱ ህዝቦች ላለፉት 20 ዓመታት ተቆራርጠው መቆየታቸውን የገለፁት አስተያየት ሰጪዎቹ በአገራቱ መሪዎች በተፈጠረው የሰላም ስምምነት መሰረት ተቋርጦ የቆየው የህዝቦቹ ግንኙነትና ተዘግተው የቆዩ በሮች መከፈት ሀሴት እንደፈጠረላቸው ነው የገለፁት። በሁለቱ አገራት መካከል ለተፈጠረው ሰላም ዘላቂነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ጭምር ነው የተናገሩት። የአስመራ ነዋሪ የሆነው መሪጌታ ሰመረ አፈወርቅ እንደተናገሩት ከርስቶስ ለአለም ሁሉ ሰላም ነው ጥሎ የሄደው ስለ ሰላም መስራት መስበክ በጣም አስፈላጊ ነው በተቻለ አቅም ስለ ሰላም ስለ አንድነት መስበክ አለብን  ፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ወንደማማቾች መሆናቸውን ያለፉትን  20 ዓመት በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸው እንዳለፈ  አሁን ግን  ሰላም በመምጣቱ ደስ ብሏናል ያሉት ቄስ ተስፋዬ ሚካኤል  ሰላሙን እንድንጠብቀው የእግዚአብሔር ቸርነት ይጨመርበት ብለዋል መምህር ሙሴ አብርሃም በበኩላቸው የመስቀል ክብረ በዓል  ልዩ ደስታ የሰጣቸው መሆኑን በተለይ የኢትዮጵያና ኤርትራ ከረጅም ዓመታት በኋላ እንዲህ ሰላም መሆናቸው የበለጠ በአሉን ልዩ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል። "ኢትዮጵያ ነበር ተወልጄ ያደኩት። ያለፈውን ትተን አሁን ባለው ነገር በጣም ተደስተናል። ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን ደግሞ ሰላምን ላመጣልን ዶክተር አብይ በጣም ነው የማመሰግነው። አሁን የሰላም አየር ነው የምንተነፍሰው ከደስታ ብዛት በአንበላ እንኳን ጠግብን በጣም ጥሩ ስሜት ነው የሚሰማን ።" ያለቸው ደግሞ  አልማዝ ገብረትንሳኤ ነች የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን በአገረ-ኤርትራ ደግሞ ልክ በበዓሉ ዕለት የደመራ ሥነ-ሥርዓቱም ጭምር በመከወን በድምቀት ይከበራል። በበዓሉ አከባበር ወቅት ኢትዮጵያና ኤርትራ የፈጠሩትን ሰላም ተከትሎ የቤተ-ክርስቲያን ዘማሪያን የሁለቱን አገራት ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ ተስተውሏል። በዓለ-መስቀልን በኤርትራ አስመራ ከተማ ሲያከብሩ ያገኘናቸው ኢትዮጵያዊንም ለተፈጠረው ሰላም ዘላቂነት የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል። "በጣም ነው ደስ ያለኝ ይሄንኑ አስበን ነው የመጣነው። ስንመጣ የመስቀል በዓልን በአስመራ ልናከብር ነው የመጣነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ በአሁን ሰዓት ሰላም ፈጥሮ በጥሩ ሁኔታ ይገኛል።" ያለው ከኢትዮጵያ የመጣው አቶ ሰውነት ጌቴ ነው ተቋርጦ የቆየው የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ዳግም በአዲስ ምዕራፍ በመጀመሩ ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች እየተገናኙ ናፍቆታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም