ቀጥታ፡

የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ17 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ማመንጨት ችሏል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በቅርቡ ወደ ኦፕሬሽን ከገቡ 16 የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች 17 ነጥብ 7 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል የፕላኒንግ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ወደ ኦፕሬሽን ከገቡ 16 የንፋስ ተርባይኖች 17 ሜጋ ዋት ሠዓት ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ 17 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት ሠዓት ማመንጨት መቻሉንም ገልጸዋል።

በጥቅምት ወር ላይ የነበረው የአካባቢው የንፋስ ፍጥነት በአማካኝ 8 ነጥብ 9 ሜትር በሰከንድ እንደነበር ገልጸው ይህም ሁሉም የንፋስ ተርባይኖች ማመንጨት በሚችሉት አቅም በቋሚነት እንዲያመነጩ እንዳደረጋቸው አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ኦፕሬሽን በገቡ የንፋስ ተርባይኖች የመነጨው ኃይል፤ ከሌሎች መሰል ጣቢያዎች የተሻለ ኃይል ማምረት እንደሚቻል ያሳየ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ የታቀደለትን የማመንጨት አቅም እንደሚያሳካ የሚያሳይ መሆኑን ያብራሩት ስራ አስኪያጇ በአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አካባቢ ያለው አማከይ የንፋስ ፍጥነት ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 48 የንፋስ ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን ከዚህ ወስጥም የ32 የንፋስ ተርባይኖች የተከላ ሥራ ተጠናቋል ማለታቸውን ከተቋሙ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም