የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ስናከብር ህዝቦቿ ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን የምንገነባበት መሰረት በማኖር መሆን አለበት

ሻሸመኔ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ስናከብር ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጎልበት ህዝቦቿ ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን የምንገነባበት መሰረት በማኖር መሆን አለበት ሲሉ የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ-ጉባዔ አቶ ኤሊያስ ኡመታ ገለጹ።

17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በሻሸመኔ ከተማ በመከበር ላይ ነው።

ቀኑን በማስመልከት በከተማዋ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ-ጉባዔ አቶ ኤልያስ ኡመታ እንዳሉት ቀኑን ስናከበር ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ኅብረ-ብሄራዊ አንድነት ስር እንዲሰድ በማድረግ መሆን አለበት።

ቀኑ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶቻችንን ይበልጥ የምናጎለብትበት አጋጣሚ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለሀገር ግንባታ በጋራ በመቆም የሕዝቦች አንድነትና ብልጽግና የተረጋገጠባት ሀገር መገንባት ይገባናል ሲሉም አንስተዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ በኅብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ዙሪያ የተዘጋጀ የውይይት ሰነድ ያቀረቡት የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በበኩላቸው አንድነትን በማጎልበት ብዝኃነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊ መስተጋብር አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ሰላምና ልማቶቻችንን በማጠናከርም ጭምር መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ አቶ አዳነ ተክለጊዮርጊስ ናቸው።

በበዓሉ ላይ ከኦሮሚያ ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የተውጣጡ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የስራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም