በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የእንስሳት ተዋጽኦ ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ

140

ጋምቤላ (ኢዜአ) ህዳር 25 ቀን 2015 በጋምቤላ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የእንስሳት እርባታን በማሻሻል ከዘርፉ ተዋጽኦ የሚገኘውን ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ጋምቤላ ከፍተኛ የቀንድ ከብት፣ የዓሳ፣ የንብና ሌሎች የእንስሳት ሀብት በስፋት የሚገኝበት ክልል መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ብሩ ገልጸዋል።

ይህን ሀብት በተገቢው ለመጠቀም እርባታውን በዘመናዊ ዘዴ በማሻሻል ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በሚቆየው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ የዘርፉን ተዋጽኦ ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

መርሃ-ግብሩ በተለይ የወተት፣ የእንቁላል፣ የማርና የዓሳ ምርታማነትን በማሳደግ በተሟላ ስርዓተ ምግብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።

በዚህም በ2014 ዓ.ም በክልሉ የወተት ምርታማነት ከነበረበት 25 ሚሊዮን ሊትር ወደ 62 ሚሊዮን ሊትር፣ የእንቁላል ምርታማነትን ደግሞ ከ13 ሚሊዮን ወደ 33 ሚሊዮን ለማሳደግ ግብ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የማር ምርትን ከአንድ ሺህ 325 ቶን ወደ ሶስት ሺህ 234 ቶን፤ የዓሳ ምርትን ደግሞ ከ132 ቶን ወደ 323 ቶን ለማድረስ መታቀዱን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቱን ለማሳደግ የታቀደው የቀንድ ከብት፣ የዶሮ ዝርያ፣ ጤናና መኖ በማሻሻል መሆኑንም ጨምረው አሰታውቀዋል።

የዓሳና የማር ምርትን ለማሳደግም የቴክኖሎጂና የግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በጋምቤላ ከተማ በዶሮ እርባታ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ወንድሙ ባልቻ በሰጡት አስተያየት፤ ከሶስት ዓመት በፊት በ200 ዶሮዎች የጀመሩት እርባታ አሁን ላይ ከሁለት ሺህ በላይ ማድረሳቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በላይ የዶሮ እንቁላልና ስጋ ምርት ለማቅረብ የሙያ ድጋፍና የብድር ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የቀንድ ከብትና የዶሮ እርባታ ከጀመሩ ወዲህ በወተትም ሆነ በእንቁላል ምርት እራሳቸውን ከመቻል አልፈው ወደ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩት የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ኮንግ ዮንግ ናቸው።

በሾፌርነት የሚተዳደረው የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ሯች ኮንግ በበኩሉ፤ የአባቱን ፈለግ በመከተል እያካሄደ ባለው የወተት ላሞች እርባታ በሚያገኘው ኑሮውን እየደጎመ መሆኑን ገልጾ ዘርፉ አዋጪ በመሆኑ በቀጣይ አስፋፍቶ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለውም ተናግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥቅምት 24/2015 ‘የሌማት ትሩፋት’ መርሃ-ግብርን በአርባ ምንጭ ከተማ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሌማት አርሶ እና አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም የሌማት ትሩፋት በቂ እና አመርቂ ምግብ ማግኘት ነው፤ በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፤ በቤተሰብ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት ያፋጥንልናል ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም