በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነርሺፕ ባህል እየጎለበተ እንዲሄድ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

135

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነርሺፕ ባህል እየጎለበተ እንዲሄድ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ገለጸ።

በስራና ክህሎት ሚኒስቴር አዘጋጅነት "ሚሊዮን ፈተናዎች፤ ሚልዮን እድሎች" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፉ የስራ ፈጣሪዎች ሳምንት "የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት" ማጠናቀቂያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በዛሬው እለት ለስራ ፈጣሪዎች የህግና ፓሊሲ ስነ-ምህዳር ምቹ ማድረግን በተመለከተ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከስራና ክህሎት ሚንስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ጋራ እንቅስቃሴ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ሚንስትሩ አክለውም የመረጃ ተደራሽነትንና አገልግሎትን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ምርምር እና የፈጠራ ስራዎች በመከወን ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢንተርፕርነርሺፕ ባህል እንዲጎለብት ዘርፉን በቴክኖሎጂ መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው የተቋማቱ የጋራ ስራዎች ለዚህ ስኬት በጥሩ ጅምር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስራና ክህሎት ሚንስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው በሁነቱ በርካታ ልምድና ተሞክሮ መገኘቱን ገልጸዋል።

"በስራ ፈጠራ ዙሪያ ከተገኘው ልምድ አንፃር መልካም ልምዶችን በማስቀጠል ተግዳሮቶችን ደግሞ እየፈታን እንሄዳለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።

አለም አቀፉ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ15ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ9ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም