በጥሎ ማለፉ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ከእንግሊዝ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

177

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 25 /2015 በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ዛሬ ከምሽቱ 4 ሰዓት በአል በይት ስታዲየም ከእንግሊዝ ጋር የምታደርገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

ሴኔጋል በምድብ አንድ በስድስት ነጥብ ኔዘርላንድስን ተከትላ ወደ ጥሎ ማለፉ መግባቷ ይታወቃል።

ሴኔጋል በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በኔዘርላንድስ 2 ለ 0 የተሸነፈች ሲሆን በሁለተኛው ጨዋታ አዘጋጇን አገር ኳታርን 3 ለ 1 ረታለች።

የቴራንጋ አንበሶች ወደ 16ት ውስጥ ለመግባት ከኢኳዶር ጋር የነበራቸውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው ነበር።

እስማይላ ሳር እና ካሊዱ ኩሊባሊ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሴኔጋል ተጋጣሚዋን 2 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

ሴኔጋል እንግሊዝን ካሸነፈች በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ሩብ ፍጻሜውን ትቀላቀላለች።

እ.አ.አ በ2002 ጃፓንና ኮሪያ ሪፐብሊክ በጣምራ ባዘጋጁት 17ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሴኔጋል በአሁኑ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢሊዩ ሲሴ አምበልነት እየተመራች ለሩብ ፍጻሜ ደርሳ የነበረ ቢሆን በቱርክ 1 ለ 0 ተሸንፋ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ አልቻለችም።

የሴኔጋል ተጋጣሚ እንግሊዝ በምድብ ሁለት በሰባት ነጥብ ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቅ ነው ለጥሎ ማለፉ የደረሰችው።

እንግሊዝ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ኢራንን 6 ለ 2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ስትረታ በሁለተኛ ጨዋታ ከአሜሪካ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይታለች።

ሶስቱ አናብስት ዌልስን 3 ለ 0 ያሸነፉበት ውጤት ወደ 16ቱ መግባታችውን ያረጋገጡበት ነበር።

ሴኔጋልና እንግሊዝ እርስ በእርስ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የ31 ዓመቱ ኤል ሳልቫዶራዊ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ኢቫን ባርቶን ተጠባቂውን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

በሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት በአል ቱማማ ስታዲየም የወቅቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ፈረንሳይ ከፖላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ፈረንሳይ በምድብ አራት በስድስት ነጥብ ምድቧን በመሪነት ያጠናቀቀች ሲሆን በአንጻሩ ፖላንድ በምድብ ሶስት በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ወደ ጥሎ ማለፉ ገብታለች።

ፈረንሳይና ፖላንድ በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ 1982 ስፔን ባሰናዳችው 12ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሁለቱ አገራት ለደረጃ ጨዋታ ተገናኝተው ፖላንድ ፈረንሳይን 3 ለ 2 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ 16 ጊዜ ተገናኝተው ፈረንሳይ 8 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ፖላንድ 3 ጊዜ ማሸነፍ ችላለች። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ቬንዙዌላዊው የ39 ዓመት ጎልማሳ ጄሱስ ኖኤል ቫሌንዙዌላ የሁለቱ አገራት ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።

የዛሬ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አሸናፊዎች ቅዳሜ ታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በሩብ ፍጻሜው ይገናኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም