የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

258

ድሬደዋ ህዳር 24/2015 (ኢዜአ) የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

የተለያዩ አካላት በተገኙበት አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "አካታች የፈጠራ ስራና ሽግግራዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች-ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ሃሳብ በድሬደዋ ከተማ ተከብሯል።

በዚሁ ጊዜ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ መንግስት በተለይ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአካል ጉዳተኞች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተቀናጁ መልኩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

እነዚህን የሕበረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ የህግ ማዕቀፎች፣ ፖሊሲዎች የሚዘጋጁና የሚተገገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁንም አካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ ተሸከርካሪዎች ማስገባት እንዲችሉ እድል ያገኙ ሲሆን ሌሎች ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞች የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል እና የእኩል ዕድል ተሳታፊ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጠቃለለ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ህግ ረቂቅ ተጠናቆ በቅርቡ ለመንግሥት የሚቀርብ መሆኑን አክለዋል።

በተያያዘም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከለጋሽ ተቋማት በተገኘ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ልዩ ልዩ የአካል መደገፊያዎች እና የትምህርት ቁሶች ለድሬዳዋ እና አካባቢው አካል ጉዳተኞች ለግሷል ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰም እንዲሁ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ተግባር ለማሳለጥ ከዚህ በፊት ተዘግተው የነበሩ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የህክምና ማዕከላት አገልግሎት እንዲጀምሩ መደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ማህበራት ፌደሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወይንሸት መልሰው በበኩላቸው ቀደም ሲል ወጥነት በጎደለው መልኩ ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች እንዲለወጡ በማድረግ ረገድ የተሻለ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

የተገኙ ለውጦችን የበለጠ ለማሳደግ በአገሪቱ በሚከናወኑ ማናቸውም ተግባራት የተቀናጀ ጥረት የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የወጡ ፓሊሲዎች እና አለም አቀፍ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለአካል ጉዳተኞች የሚስማሙ መሠረተ ልማቶችን ምቹ እና ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እየሰራ መሆኑንም ተናግርዋል።

በተጨማሪም በአገልግሎት አሰጣጥ እና በከተማ ልማት አካል ጉዳተኞች የተካተቱበት እና የሚጠቀሙበት እንዲሆን በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን ሰዎች በተለያዩ መልኩ አካል ጉዳት እንዳላቸው መረጃዎች ያመልከታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም