ሙስና - የሞራል ዝቅጠትና የአገር ጠልነት ማሳያ

808

በአየለ ያረጋል

 

ሙስና ዐይን አወጣ - Addis Maleda

በአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት 'ሙስና' መቅሰፍት ነው። ጥፉ፣ ብልሹ፣ ግም እና በመሰል ነውርን በሚገልጡ ቃላት ይተረጎማል። አለቃ ኪዳነወልድ ቀጥለውም ሙስናን 'መበስበስ፤ ጥፉነት፣ ጥፋት፣ መከራ'... እያሉ ይፈቱታል። ሙስና በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሀጢያት፣ በዓለማዊ ሕጎች ወንጀል የሆነ፣ በማህበረሰቡ ቀደምት ብሂሎች ውግዝ ነው። በፈላስፎችና በማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን በዘቀጠ እሴት መገለጫነቱ፣ ተያይዞ ገደል እንደሆነ ያነሳሉ።

ኦክስፎርድ መዝገበቃላትም ሙስናን (Corruption) ከአለመታመን/እምነትን ከማጉደል፣ ምግባረ ቢስነት፣ ጉበኝነት እና በመሰል ቃላት ይገልጸዋል። ከዝቅጠትና ከመቆርቆዝ ጋር ያቆራኘዋል።

የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ አርስቶትል፣ ሊሰሮ፣ ማኪያቬሊ የተሰኙ ፈላስፎችን በመጥቀስ የነገረ-ሙስናን ትንታኔ ባቀረቡበት አንድ ጽሁፍ ሙስና የማህበረሰቡን የሞራል፣ የሕግና ፍትሕ እሴቶች ይንዳል፤ የፖለቲካ ብክለት መገለጫ ነው፤ የነባር ግብረ ገባዊ እሴቶች መናድ ማሳያ ነው፤ ለማኅበረሰብ ሕልውና አደጋ ነው፡፡ እናም ሙስና ምቾት፣ ቅምጥልነትና ራስ ወዳድነት መንፈስ የተጠናወተው እኩይ ምግባር መላበስ ነው። በጥቂቶች ብዙሃኑን የሚበክል ድርጊት ነው። እናም ኢ-ፍትሐዊነት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅነት፣ ሥርዓተ ነውረኝነት፣ አድልዎ እና የሞራል ዝቅጠት እንዲለመዱ ያደርጋል ይላሉ።

ጥናቶች ሙስናን በተለያዩ ደረጃዎችና መልኮች ይገልጹታል። መጠነ ሰፊ ሙስና፣ አነስተኛ ሙስና፣ ፖለቲካዊ መስና እና ስልታዊ ሙስና በሚል ይመደባሉ።

መጠነ ሰፊ ሙስና (Grand Corruption) ከፍተኛ የመንግስት ሹመኞች የህዝብ የሆኑ ሀብቶችን ለራሳቸው ጥቅም ለማመቻቸት የመንግስትን ፖሊሲ እና አሰራር በማዛባት የሚፈጸም ነው። ይህ የሙስና አይነት በአንድ አገር መልካም አስተዳድር ለማስፈን፣ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረግን አካሄድ ይገዳደራል።

ጥቃቅን ወይም አነስተኛ ሙስና (petty corruption) በታችኛው የመንግስት መዋቅርና በመከከለኛ ደረጃ ያሉ የመንግስት ሹመኞችና ሰራተኞች ከህዝብ ጋር በሚኖራቸው አገልግሎት አሰጣጥ ኅላፊነትን በመተው ለግል ጥቅም በመሻት የሚፈጸም ነው። በጤና፣ በትምህርት፣ በጸጥታና በሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ዘንድ መደበኛ ስራቸውን ለማከናወን ተጨማሪ ክፍያ ወይም ጉቦ መጠየቅ የዚህ ሙስና ማሳያ ነው። እናም ጉቦ፣ ስርቆት፣ ማጭበርበር፣ የተገልጋዮች ላይ አድልዎ መፈጸም የመሳሰሉትን የሙስና ተግባራትን ያካትታል። በርግጥ እነዚህ ድርጊቶች እንደ ገንዘቡ መጠን ስፋት ሁኔታ ተመዝነው በመጠነ ሰፊ ሙስና ምድብ ሊካተቱ ይችላሉ።

ሌላው ፖለቲካዊ ሙስና /Political corruption/ ነው። ይህ ሙስና በፖለቲካ ውሳኔ ሰጭዎች አማካኝነት የሚፈጸም ነው። ይህም ፖለቲካ ውሳኔ ሰጭዎች ስልጣናቸውን ለማስቀጠል፣ ገጽታቸውን ለመገንባት፣ ሀብት ለማካበት በመፈለግ ተቋማትንና ህጋዊ አሰራሮችን በራሳቸው መንገድ የሚቀርጹበት ሂደት ነው።

ስልታዊ/ስርዓታዊ /Systemic corruption/ ሙስና አይነት ደግሞ ማህበረሰቡ በመላ ማንኛውንም ጉዳይ ለመከናወን ሙስናን እንደ መደበኛ ስርዓት የሚወስድበት አጋጣሚ ሲፈጠር ነው። ይህም አብዛኛው የመንግስት ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ በሙስና አሰራሮች የተተበተበ እና አብዛኘው ተገልጋይ አማራጭ በማጣት በተደራጁ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖችን ኮቴ በማሽተት የሚሄዱበት ሁኔታ ነው።

ስርዓታዊ ሙስና ተቋማትን እንዲሁም በፖለቲካዊና ማህበረ ምጣኔ ስርዓት ላይ የተቀመጡ ግለሰቦችን ባህሪም የሚጎዳ ነው። እንዲህ አይነት ሙስና በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ስር የሰደደ፣ ወጥ፣ የተደራጀና ለማስወገድ የሚከብድ ይሆናል።

ሙስና በግል እና በህዝብ ተቋማት ውስጥ በተለያየ መልኩ ይፈጸማል። በመንግስት ተቋማት ዘንድ እንደሚዘወተር በብዛት ቢገለጽም ከአነስተኛ አገር በቀል እስከ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑና በግል ድርጅቶችም የከፋ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህም የገበያ ስርዓቱን ያቃውሳል፤ የማህበረሰቡን ኑባሬ ይበክላል።

ሙስና ድህነትን ያባበሳል፤ ሰብዓዊ መብትና ክብርን ይገፋል፤ አካባቢን ይሸረሽራል፤ ዕድገትን ይጎትታል፤ ውስጣዊና በአገራት መካከል ግጭት ይቀሰቅሳል፤ የመንግስትን ቅቡልነት እና ዴሞክራሲ ይፈታተናል።

መልኩ ምንም ይሁን ምን ሙስና ጠንክሮ መስራትን የሚኮንን፣ ሳይሰሩ መብንላትን የሚያጀግን፣ የአጋርነትን ሞራል የሚሰብር፣ ሀገርን ለውጫዊ ደህንነት ስጋት አደጋ የሚጥል፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያቀጭጭ፣ ውስጣዊ ስርዓትና መረጋጋትን የሚፈትን፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና አጠቃላይ ዘላቂ ልማትን የሚገታ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት ሙስና 'በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ' ሆኗል።

ኢትዮጵያን ለስጋት የዳረገው ሙስና

ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት የሙስና ፈተና በኢትዮጵያ በሚፈለገው ልክ የውይይት አጀንዳ እንዳልነበር ይነሳል። ይህም ሙስና በአጠቃላይ ማህበራዊ ኑበሬ እና ንግድ ስርዓት ውስጥ የሚኖረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በቅጡ ካለመገንዘብ ሊሆን ይችላል የሚሉ ጥናቶች አሉ። በጉዳዩ ላይ አለመወያየት፣ የመረጃ ልውውጥ አለመዘርጋት እና አለመከራከር ችግሩ ስር እንዲሰድ አድርጓል የሚሉም አሉ።

ሙስናን ጥዩፍ የነበሩ አባባሎች እየጠፉ፤ በቀልዳቀልድ መልኩም ቢሆን ሙስናን የሚያበረቱ ንግግሮች እየተለመዱ መጥተዋል። ከላይ ከተጠቀሱ የሙስና አይነቶች ኢትዮጵያን የትኛው ሙስና ምድብ የበረታባት ይሆን? መጠነ ሰፊ፣ ስርዓታዊ፣ አነስተኛ ወይስ ፖለቲካዊ ሙስና የሚለው ለአንባቢ ትዝብት የሚተው ነው።

የፌደራል ስነምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ሀብት ያላስመዘገቡ አመራሮችን እና ባለሙያዎችን የጠቆመ ዜጋ ከተጠቆመው ሀብት 25 በመቶ እንዲያገኝ እንደሚደረግ መግለጹ አይዘነጋም። ይህም የሆነው በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሰረት ሁሉም የመንግስት ሹመኛ ሀብቱን ማሳወቅ ሲኖርበት አፈጻጸሙ በሚፈለገው ደረጃ ባለመከናወኑ ነው። በኮሚሽኑ መረጃ እስካሁን 763 የመንግስት አመራሮች ቢለዩም፤ እስካሁን ሀብታቸውን ያስመዘገቡት 20 በመቶው ብቻ ናቸው።

ሙስና በኢትዮጵያ ከኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት ቀጥሎ የአገር ደህንነት ስጋት መሆኑ በመንግስት ይፋ ሆኗል። በተለይም ኢትዮጵያ አጋጥሟት የነበረውን ፈተና እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መንግስት ቀይ መስመር ያለውን ሌብነት ሙሰኞች ቀይ ምንጣፍ በማድረግ ሲረማመዱበት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መናገራቸው ይታወሳል።

ስር የሰደደ፣ ህዝብ ያማረረና ለአገር የደህንነት ስጋት የሆነውን ሙስና ለመግታትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። የኮሚቴው ሰብሳቢና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነህ እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ኮሚቴው ከተዋቀረ አንስቶ ባሉ ክንውኖች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመንግሥት አግልሎት አሰጣጥ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በፋይናንስና ግዥ፣ በመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦት ዘርፎች ላይ ሙስና በስፋት እንደሚስተዋል ገልጸዋል። በፀጥታና ፍትህ ተቋማት ዘንድም በተመሳሳይ ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም በአቋራጭ የመበልፀግ የሙስና ወንጀሎች በስፋት እንደሚስተዋሉም እንዲሁ።

የኮሚቴው ሰብሳቢና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነህ መንግስት ሙስናን ለመከላከል የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ ቢቆይም በኮሮና ወረርሽኝ እና በጦርነት ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ችግሩን መቅረፍ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው የተቋቋመው የሁሉም ተቋማት መረጃ ወደ አንድ ቋት መጥቶ እንዲሰራበት በማስፈለጉ መሆኑንም አንስተዋል።

ብሔራዊ ኮሚቴው የሕግ፣ የፋይናንስና የመረጃ ሶስት ንዑስ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ስራ መጀመሩን ገልጸው፤ የመረጃ መቀበል ስርዓት መዘርጋትና በየተቋማቱ የተሰሩ ጥናቶች የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን አመልከተዋል።

በዚህም በህዝብ ጥቆማ እና በጥናት በተለዩ ዘርፎች በሌብነት ወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ተግባራዊ እርምጃ መወሰድ መጀመሩንም ተናግረዋል።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ በበኩላቸው የመሬት አስተዳደር፣ የፀጥታና ፍትህ፣ የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

በተለይ በመሬት አስተዳደር፣ በፍትህና በፀጥታ ተቋማት  ላይ ተግባራዊ እርምጃ እየተወሰደ  እንደሆነም አንስተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደር ልጅ እና የልማት ተነሺ ያልሆኑ አካላትን ስም በመጠቀም መሬት እና ገንዘብ የመዘበሩ፤ በሀሰተኛ ሰነድ የኮንዶሚኒየም ቤት የወሰዱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት።

በማጭበርበር ወንጀል የተወረሩ መሬቶችን መታገዳቸውን እና ሀብት የማስመዝገብ ግዴታቸውን ወደጎን ትተው አለአግባብ ሃብት በማካበት የተጠረጠሩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

በፍትህና ፀጥታ ተቋማትም ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ከግለሰቦችና ድርጅቶች ገንዘብ ለመቀበል የተንቀሰቀሱ የስራ ኃላፊዎችም ተለይተው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአብነትም የፋይናንስ ድህንት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በመረጃና መረብ አስተዳደር እንዲሁም በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሚሰሩ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ቁጥጥር ስር እንደዋሉም ገልጸዋል።

ቀደም ብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ የፍትህና ጸጥታ ተቋማት ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ክስ የመመስራት ተግባራት እየተካሔደ መሆኑን ተናግረዋል። በወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አንስተዋል።

በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ250 በላይ ጥቆማዎች በተለያዩ መንገዶች ቀርበው ማጣራት እየተከናወነባቸው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በክልሎችም ከትንሽ እስከ ከፍተኛ የተደራጀ ሌብነት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በመለየት ተጠያቂነትን የማስፈኑ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመሆኑም በተለያዩ የተደራጁ ወንጀሎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ከወንጀል ተጠያቂነት ባለፈ በሙስና ያፈሩት ሃብት እንዲወረስና ያሸሹት ደግሞ እንዲመለስ በማደረግ ህጋዊ  ርምጃ ይወሰድባቸዋል።

ወደ ውጭ አገራት ሀብታቸውን ያሸሹ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተም፤ ሀብት ለማስመልስና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከአገራት ጋር ስምነት በመደረጉ ይሕን መነሻ በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴው አባልና የፌደራል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙስና አገር ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የጸረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ መረጃዎችና ጥቆማዎች ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ሲሰበሰቡ መቆየታቸውን ጥቅሰው፤ እስካሁን ባለው ሂደት 250 መረጃዎች ተለይተው ለምርመራ ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ መንግስት የጀመረው የጸረ ሙስና ትግል ሀገርን ከዘረፋ የማዳንና ብሔራዊ ደህንነቷን የማረጋገጥ ትግል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ትግሉ ህዝባዊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ህብረተሰቡም ሙስንና በመጸየፍ እና ሙሰኞችን በመቆጠም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎች በተከታታይ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ የገለጸው ኮሚቴው፤ ህብረተሰቡ በ9555 በአጭር መልዕክት ጥቆማውን እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።

በርግጥም ሳይሰሩ መብላትን የሚያጀግነው፣ የዘቀጠ እሴት መገለጫ የሆነው፣ ሀገርን ለደህንነት ስጋት የሚዳርገውና ዘላቂ ልማትን የሚገታውን ሙስና በአንድነት መግታት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም