መንግስት ሙሉ አቅሙን በመጠቀም ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ ነው - የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ

21

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 24/2015 መንግስት በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ) የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የገንዘብና ሀብት አሰባሰቢ ክፍል ዳይሬክተር ሊዛ ዳውተን ተናገሩ።

የኦቻ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የገንዘብና ሀብት አሰባሰቢ ክፍል ዳይሬክተር ሊዛ ዳውተን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ዳሰሳ ሪፖርትን በአዲስ አበባ ይፋ አድርገዋል።

በሪፖርታቸውም በዓለም ላይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልገው ህዝብ ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።

ኦቻ በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ለስደተኞች አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እያደረገ መሆኑን እንገነዘባለን ነው ያሉት።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍን ተደራሽ ለማድረግ እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን አድንቀዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ችግሮች ለተጎዱ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናከሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ዳይሬክተሯ፤ ከዚህ አኳያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀጣይ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ችግር በሌላው የዓለም ክፍል ያለ ችግር መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤  የጋራ ችግርን በጋራ መመከት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም