በዋግ ኽምራ 231 ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማቋቋም የመማር ማስተማር ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል

94

ሰቆጣ  (ኢዜአ) ህዳር 24 ቀን 2015 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በጦርነቱ ተጎድተው የነበሩ 231 ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማቋቋምና በማደራጀት የመማር ማስተማር ስራ እንዲጀምሩ መደረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍትሃለሽ ምህረቴ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በጦርነቱ  260 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛና መካከለኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል 239ኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፤   21ዱ ደግሞ  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በትምህርት ቤቶቹ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮችን ጨምሮ ለመማር ማስተማር ስራው አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ቁሳቁስና መሳሪያዎች  መውደማቸውን አስታውሰዋል።


ህብረተሰቡን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ለትምህርት ቤቶቹ መለስተኛ የመልሶ የማቋቋም ሥራዎችን በማከናወንና በትምህርት ቁሳቁስ በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልፀዋል።


ወይዘሮ ፍትሃለሽ አክለውም ባለድርሻ አካላት በትምህርት ቤቶቹ  የሚስተዋለውን የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

ምክትል ኃላፊዋ እንዳሉት በዞኑ በአሁኑ ወቅት በ211 የአንደኛ እና  በ20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  100 ሺህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው።

በዞኑ ሁለት ወረዳዎች  የመማር ማስተማር ስራው በተመሳሳይ ለማስጀመር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ ዝቋላ ወረዳ የቅዳሚት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ምስጋናው በላይ እንዳሉት፤ በጦርነቱ በትምህርት ቤቱ ላይ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም በተደረገው ጥረት የትምህርት ስራውን መልሶ እንዲቀጥል ተደርጓል።


በባለድርሻ አካላት ትብብርና ድጋፍ መልሶ የተቋቁመው ትምህርት ቤት 278 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው ብለዋል።


በትምህርት ቤቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪው አለነ ሙላው ትምህርት በመጀመሩ መደሰቱን  ገልጾ፤ ትምህርት ቤቱ የቤተ ሙከራና የኮምፒውተር ተግባራዊ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችለው ድጋፍ ያስፈልገዋል ብሏል።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር  ዞን  298 የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም