ቀጥታ፡

አርሶ አደሩ ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ ገበያ ተኮር ምርት በጥራትና በብዛት እንዲያመርት እየተሰራ ነው

አዳማ (ኢዜአ ) ህዳር 24/2015 አርሶ አደሩ ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ ገበያ ተኮር ምርት በጥራትና በብዛት እንዲያመርት ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች የተሻለ ቴክኖሎጂና ፓኬጅተጠቅመው ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ መድረክ ተካሂዷል።

በኮሚሽኑ የህብረት ስራ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ዲርባ በቀለ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በመገንባት የአርሶ አደሩን የአስተራረስ ዘይቤ ማዘመንና ገበያን መሰረት አድርጎ እንዲያመርት እየሰራን ነው ብለዋል።

በአርሶ አደሩ መካከል ተወዳዳሪነት እንዲጎለብትና የግብርና ምርቶች በእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዩኒየኖች የዘይትና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካን በማቋቋም ጥሬ የግብርና ምርትን ወደ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምረውበት በማቅረብ ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

የእርሻ ስራ ንግድ እንዲሆን አርሶ አደሩ ዘንድ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ብሎም ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ ገበያ ተኮር ምርቶችን በጥራትና በብዛት እንዲያመርት ቱስኬል ከተባለ ድርጅት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል።

የከሰም ዩኒዬን ስራ አስኪያጅ አቶ አማከለ ዘውዱ በበኩላቸው ማህበሩ ከድርጅቱ ጋር በመካናይዜሽን፣ምርትና ምርታማነታችን ማሳደግ የሚችሉ የአፈር ማዳበሪያና ፀረ አረም ኬሚካል አጠቃቀም፣በተፈጥሮ ማደበሪያ ዝግጅት ላይ በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከድርጅቱ ጋር በአርሶ አደሩ ግንዛቤ ፈጠራ፣በግብዓትና አጠቃቀምና ገበያ ተኮር ምርቶች ማምረት በሚቻልበት መስራት ከጀመርን በኋላ ከሁለት ዓመታት በፊት 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የነበረ የዩኒዬኑ ካፒታል በአሁኑ ወቅት 68 ሚሊዮን ደርሷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቱስኬል ስራ አስኪያጅ አቶ ተካልኝ አያና በበኩላቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የስነ ምግብ ስርዓቱን ለማዳበር ከኮሚሽኑ፣ዩኒዬኖችና መሰረታዊ ማህበራት ጋር ሆነን በአርሶ አደሩ አቅም ግንባታ ላይ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ለምርትና ምርታማነታቸው እድገት፣ገበያ ተኮር እርሻ እንዲስፋፋና የግብርና ስራ የአካባቢውን ስነ ምህዳር በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ለአርሶ አደሮች የአቅም ግንባታና አካታች የንግድ ስራ ስልጠና እየሰጠን እንገኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም