የአራት የዓለም ክብረ ወሰኖች ባለቤት አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን ልትወዳደር ነው

707

አዲስ አበባ ሕዳር 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) አትሌት ለተሰንበት ግደይ የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎዋን ነገ በስፔን በሚካሄደው የቫሌንሺያ ማራቶን ታደርጋለች።

በመም፣ በጎዳና ላይ ሩጫ እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ስኬታማ ድሎችን ያገኘችው አትሌት ለተሰንበት አሁን ደግሞ ፊቷን ወደ ማራቶን አዙራለች።

ለ42ኛ ጊዜ በሚካሄደው የቫሌንሺያ ማራቶን ውድድር ማራቶንን አሀዱ ብላ ትጀምራለች።

አትሌት ለተሰንበት እና ቫሌንሺያ ከተማን በአትሌቲክሱ ስኬቷ ውስጥ ነጣጥሎ ማየት የሚቻል አይደለም።

በእስከ አሁኑ የአትሌቲክስ ቆይታዋ ሁለት የዓለም ክብረ ወሰኖችን የሰበረችው በቫሌንሺያ ከተማ ነው።

እ.አ.አ በ2020 በቫሌንሺያ በተካሄደው የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር 14 ደቂቃ ከ6 ሴኮንድ ከ62 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በታዋቂዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን በአምስት ሴኮንድ አሻሽላለች።

ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ወደ ስፔን በመመለስ በቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን 1 ሰአት ከ2 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ በመግባት በኬንያዋ አትሌት ሩት ቼፕጌቲች ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን በአስደናቂ ብቃት በ110 ሴኮንዶች በማሻሻል ዓለምን ጉድ አስባለች።

አትሌት ለተሰንበት ውድድሩን ያሸነፈችበት መንገድ “በዓለም የረጅም ርቀት ውድድር ታሪክ ከታዩ አስደማሚ ብቃቶች አንዱ ነው” የሚል በወቅቱ በአትሌቲክሱ ማህበረሰብና ባለሙያዎች ዘንድ ትልቅ አድናቆት ያስቸራት ነበር።

አትሌቷ ነገ ወደ ቫሌንሺያ በድጋሚ ስትመለስ በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጂድ ኮስጌይ 2 ሰአት ከ14 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ የተያዘውን የሴቶች ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ለመስበር ትሮጣለች።

አትሌት ለተሰንበት ግደይ የ10 ሺህ ሜትር እና 15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ክብረወሰንም ባለቤት ነች።

አትሌት ለተሰንበት በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታውስ ነው።

አትሌት ሱቱሜ አሰፋ፣አትሌት እታገኝ ወልዱና አትሌት ቲኪ ገላና በነገው የቫሌንሺያ ማራቶን በሴቶች ከሚሳተፋ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ይገኙበታል።

ኬንያዊቷ አትሌት ሼይላ ቼፕኪሩይ በውድድሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ትፈትናለች የሚሉ ዘገባዎችን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በዘገባዎቻቸው አውጥተዋል።

በወንዶች በሐምሌ ወር በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው አትሌት ታምራት ቶላ ይጠበቃል።

አትሌት ጌታነህ ሞላ፣አትሌት ዳዊት ወልዴና አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ በውድድሩ ከሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ይገኙበታል።

ኬንያዊው አትሌት ጆናታን ኮሪር ውድድሩን ያሸንፋሉ የሚል ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም