በ180 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበርና ስደተኞችን እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

17

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 24/2015  በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በ180 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበርና ስደተኞችን ብሎም የሚጠለሉበትን አካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሁለተኛው ዘር የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ የግብርና  ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የልማት አጋሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት  በተገኙበት በአዳማ  ከተማ  ነው ይፋ የሆነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በተለያዩ ምክንያት ወደ  ኢትዮጵያ የገቡ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች  በሚኖሩበት  አካባቢ ሊከሰት የሚችልን ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚረዳ  ነው፡፡

የግብርና  ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን  እንደተናገሩት፤ በመጀመሪያው  ዙር  የፕሮጀክቱ  ትግበራ ስደተኞችን ያስጠለሉ የማህበረሰብ  ክፍሎችን የልማት  ችግሮች ያቃለሉ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በአፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሱማሌና በትግራይ ክልሎች ከ2009 ዓ.ም  ጀምሮ የተከናወኑ  የልማት ስራዎች ውጤት እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል።

ለአብነትም 225 የአንደኛ  ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 98 የጤና ኬላዎች፣ 48 የእንስሳት  ጤና ኬላዎች፣ 520 ኪሎሜትር የገጠር መንገድ፣ 220 የንጹህ  መጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በፕሮጀክቱ  ከተከናወኑ  ተግባራት መካከል ይገኙበታል ነው ያሉት።

በተጨማሪም  አራት የግብርና  ግብዓት ማከማቻ  መጋዘንና አምስት አነስተኛ  የገበያ  ማዕከል ማዕከላት መገንባታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አንስተው በመጀመሪያው  ዙር የፕሮጀክቱ  ትግበራ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ  ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው ሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት  180 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት ሲሆን ለሚቀጥሉት አምስት  ዓመታት እንደሚተገበርና የገንዘብ ድጋፉ ከዓለም  ባንክ የተገኘ መሆኑ  ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ስደተኞችን የሚያስጠልሉ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ  ከማድረግ  ባለፈ በቀጥታ  ስደተኞችን ተጠቃሚ  የሚያደርግ በመሆኑ ከመጀመሪያው  ዙር የተለየ  እንደሚያደርገው ተመልክቷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በመጀመሪያው ዙር የፕሮጀክቱ ትግበራ የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ  ችግሮችና ቀጣይ  ስራዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም