የኦሮሚያ ክልል በሙሰኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ ነው

154

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 24 ቀን 2015 በኦሮሚያ ክልል በሙሰኞች ላይ ጠንካራ ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፉት ሶስት ወራት የሙስና ወንጀል የፈጸሙ አካላት ላይ የተወሰደ እርምጃ አስመልከቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ጉዮ ዋሪዮ በሰጡት መግለጫ ባለፉት ሶስት ወራት ከ1 ሺህ 300 በላይ ግለሰቦች የሙስና ወንጀል መፈጸማቸው ተረጋግጦ ጉዳያቸው ውሳኔ አግኝቷል።

በዚሁ መሰረት እያንዳንዱ የወንጀሉ ተሳታፊ ከአንድ ዓመት ከ6 ወር እስከ 16 ዓመት በሚደርስ ዕኑ የእስራት እንዲቀጡ እንደተፈረደባቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም በተለያዩ ከተሞች ከ230 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት፣ 70 ሚሊዬን ብር፣ ሶስት የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና ሶስት መኖሪያ ቤቶች ለመንግሥት ገቢ ተደርገዋል ብለዋል።

እንደ ዐቃቤ ሕግ ጉዮ ገለጻ ባለፉት ሶስት ወራት 285 ከሙስና ጋር የተያያዙ መዝገቦች ላይ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፤ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ 67 ሚሊዮን ብር ታግዷል።

በተጨማሪም 289 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት፣ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ሰባት መኖሪያ ቤቶችና ሶስት ተሽከርካሪዎች ታግደው ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መሬት አስተዳደር፣ የመንግሥት ግዥና ጨረታ ዋና ዋና ለሙስና ወንጀል ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በሙስና ወንጅል ተሳትፈው የተገኙትም መሓንዲሶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሃብቶችና ደላሎች መሆናቸውንም አቶ ጉዮ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ሙሰኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ገልጸው፤ የክልሉ ሕዝብ መንግሥትን በቅርበት እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም