ኢትዮጵያ ለዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ድህነትን ለመቀነስ እየሰራች ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ድህነትን ለመቀነስ እየሰራች ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 ኢትዮጵያ ለዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ድህነትን ለመቀነስ እየሰራች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ላለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው በ17ኛው የበየነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
በንግግራቸውም ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ድህነትን ለመቀነስ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ የዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ የራሷን አስተዋጽኦ ማበርከቷን አስታውሰው፤ በቀጣይም ተሳትፎዋንና አጋርነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው ለጉባኤው ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በጉባኤው በአካልና በበይነ መረብ አማካኝነት ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ከ300 በላይ ውይይቶች በስኬት ተካሂደዋል ነው ያሉት፡፡
በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዜጎች የኢንተርኔት ተደራሽ አለመሆናቸውን ጠቁመው የኢንተርኔት ተደራሽነት የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ የኢንተርኔት ተደራሽ ማድረግ የጉባኤው ዋነኛ መልእክት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡