የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሁሉም አካላት ርብርብን ይፈልጋል-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ

206

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ህዳር 23 ቀን 2015 በሀገሪቱ በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ አየለች እሼቴ ተናገሩ።

"አካታች የፈጠራ የስራና ሽግግራዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ሃሳብ የአለም የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በድሬዳዋ እየተከበረ ይገኛል።

በአካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያተኩረው ውይይት ላይ ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ እንደተናገሩት መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ መብቶች በአግባቡ እንዲተገበሩ በትኩረት ይሰራል፡፡

ለዚህም የአካል ጉዳተኞች ማህበራትን በፋይናንስና በስልጠና እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከጠባቂነት ተላቀው በራሳቸው አቅም እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ይሰራል ብለዋል።

ውይይቱ አካታች ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር ብሎም አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካዊ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው ያመለከቱት።

በተለይ ሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በወጥነት በስርዓት እንዲመራና የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎችን አጠናቆ ወደ ተግባር ለመለወጥ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የሚፈለገው መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ የሁሉም አካላት ተሳትፎና የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ  ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ ሁሴን፤ በአስተዳደሩ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችና ማህበራቱን በሁሉም መስክ ተደራሽና ተካታች የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በውይይቱ የተንፀባረቁ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በመጠቀም በቀጣይ የተሻለና የተቀናጀ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ቀኑ ለተገኙ ለወጦች ዕውቅና የሚሰጥበትና ለተስተዋሉ ችግሮች ደግሞ መፍትሔ የምናመለክትበት ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው።

የውይይቱ ተሳታፊ አካል ጉዳተኛ ወይዘሮ ፈሰሱ አገሸ  እንዳሉት፤ በየዓመቱ የሚታዩት ለውጦች ለአካል ጉዳተኞች ተስፋ ሰጪ ናቸው።

ሆኖም አሁንም ሁላችንም ለመብቶቻችን መከበርና ለተሻለ ለውጥ ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል።

በሌላ በኩል የአለም የአካል ጉዳተኞች ቀን አከባበር ላይ ለመሳተፍ  የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ድሬደዋ የገቡ ሲሆን የድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች አቀባበል አድርጎላቸዋል።

የአለም የአካል ጉዳተኞች ቀን ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም