ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በደምቢዶሎ ከተማ ከህዝብ ጋር ውይይት ያደርጋሉ

72
አዲስ አበባ ግንቦት12/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በደምቢዶሎ ከተማ ከህዝብ ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት እንደሚያደርጉ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ። በእለቱ በከተማዋ የተገነቡት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ይመርቃሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት የደምቢዶሎን ህዝብ እንደሚያወያዩ ይጠበቃል። ጊዜው መንግስት ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማስመዝገብ የሚችልበት ምቹና ለህዝቡ ችግር ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጥበትና ለመፍትሄውም የህብረተሰቡን ሙሉ ተሳትፎ የሚፈልግ አመራር መፈጠሩን የሚያመላክት መሆኑን ነው ዶክተር ነገሪ የጠቆሙት። ቀድሞ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት የምትታወቀው የደምቢዶሎ ከተማ በልማት የሚፈለገውን ያህል እንዳልተራመደች የገለጹት ዶክተር ነገሪ ከተማዋ በተፈጥሮ የተቸራትን ዕምቅ ሃብት ወደ ልማት ለመቀየር የዩኒቨርሲቲው መገንባት ለህዝብ  ጥያቄ ትልቅ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በከተማዋ ተገኝተው ከህዝቡ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ለቀጣይ የልማት ስራዎች መንገድ የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል። የደምቢዶሎ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በኃላፊዎቹ መምጣት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው "ለሚያነሱት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኙ" ተስፋ ማድረጋቸውን ለኢዜአ ሪፖርተር ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም