የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚጠቅሙ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል-አቶ መላኩ አለበል

118

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ለአምራች ኢንዱስትሪው የሚጠቅሙ የየሀገራቱን የእውቀትና ቴክኖሎጂ ልምድ በማምጣት ረገድ በትኩረት እንዲሰሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ጥሪ አቀረቡ።

በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቁቁ ዲፕሎማቶች ገላንና ዱከም ከተሞች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።     

የጨርቃጨርቅ፣ ብረታብረት፣ መድሃኒት ፋብሪካዎች እንዲሁም የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻና መሸጫ ኢንዱስትሪዎች ዲፕሎማቶቹ ከጎበኟቸው መካከል ይገኙበታል።  

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከአምራች ዘርፉ 9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳ እየሰራች ነው።

በዘርፉ ምርታማነትን በ85 በመቶ ማሳደግ እንዲሁም ለ5 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል የመፍጠር ግቦች መያዙን ጠቅሰው፤ ለስኬታማነቱ ብዙ ስራ ይፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት ከፍ ሊል እንደሚገባ ጠቁመው በዚህ በኩል የዲፕሎማቶች ድርሻ የላቀ መሆኑን አብራርተዋል።     

የገበያና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለዘርፉ ሌላው ፈተና መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ዲፕሎማቶች ችግሩን በማቃለል ረገድ ሊያግዙ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።   

አምራች ዘርፉ ላይ ያለው የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ክፍተት እንዲፈታ ዲፕሎማቶች በተመደቡባቸው ሀገራት ያለውን ልምድና ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በጉብኝቱ ከተሳተፉ ዲፕሎማቶች መካከል ዶክተር ዘሩባቤል ጌታቸው አዳዲስ የገበያ መዳራሻዎችን ማስፋት ላይ እንደ ዲፕሎማት የሚጠበቅብኝን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

የውጭ ባለሃብቶችን መሳብም ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል።

ከስልጠናው በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል ያደረግነው ጉብኝት ቀጣይ ለምንሰራው ሥራ ስንቅ የሚሆን ነው ያሉት ደግሞ ዲፕሎማት ሮባ ደሜ ናቸው።     

መንግሥት እየተገበራቸው ያሉ የልማት ፖሊሲዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

ሌላዋ ዲፕሎማት አብረኸት መሃሪ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የሚያመጧቸው ባለሃብቶች ስኬታማ የስራ ጊዜ እንዲያሳልፉ ድጋፍና ክትትሉ ሊጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም