በመልሶ ግንባታ፣ ማቋቋምና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም - ኢዜአ አማርኛ
በመልሶ ግንባታ፣ ማቋቋምና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፋችንን እናጠናክራለን- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 በመልሶ ግንባታ፣ ማቋቋምና የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፋችንን እናጠናክራለን ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አስታወቀ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ዕቅዶች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጨምሮ ገልጿል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ እና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጦርነት፣ በኮቪድ-19፣ በድርቅና በሌሎችም ከፍተኛ ውጫዊ ጫናዎች ቢፈተንም እድገት ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል፡፡
እድገቱ መጠኑንና ፍጥነቱን ጨምሮ ለማስኬድም መንግስት የተለያዩ ስራዎችንና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
ለዚህም እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ያሉ የልማት አጋሮች ድጋፍ ይፈለጋል ነው ያሉት፡፡
"ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ችግሮች ሁሉ በላይ ናት" ያሉት ዶክተር ፍጹም አሰፋ የልማት አጋሮችም የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት በመደገፍ አጋርነታቸውን በማረጋገጥ ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያሉባትን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመቅረፍ በየጊዜው የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑን ገልጸው አሁንም 2ኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የገቢና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን፣ የሸቀጦች ዋጋ መናር እና ሌሎች ችግሮችም ኢኮኖሚው ላይ መኖራቸውን እንደጠቀሱ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በሚደረገው ሪፎርም ችግሮቹን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምም ለዚህ ስኬታማ ስራ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሃላፊ አኪም ስታይን በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መሃከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
በመልሶ ግንባታ፣ ማቋቋምና በተለያዩ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ቤተሰብ ነው ያሉት ኃላፊው ይህ የልማት አጋርነት እየጎለበተ እንደሚሄድ መናገራቸው ተመላክቷል።